
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ 9ኛ መደበኛ ስብሰባውን ነገ ይካሄዳል።
ምክር ቤቱ በነገ ስብሰባው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና መንግሥት መካከል የተደረገውን የወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ እና በሁለቱ መንግሥታት መካከል የተደረገውን ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የህግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁቹን ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
እንዲሁም ምክር ቤቱ ፣ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በብራዚል ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የተደረገውን ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ የህግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን ያፀድቃል ተብሎም ይጠበቃል።
በተያያዘም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና በደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ መንግሥት መካከል የተደረገዉን በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የህግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀርበውን ሪፖርትና ውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ረቂቅ አዋጁን የሚያፀድቅ ይሆናል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በኮሪያ ኤክስፖርት -ኢምፖርት ባንክ መካከል ለህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ፕሮጀክት ምዕራፍ 2 ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ጨምሮ ፣ የህብረት ስራ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፣ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኩዩሪቲ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን እና የፌዴራል የስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የሚመራ ይሆናል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
