ህብረት ስራ ማህበራት በመሰረታዊነት የአርሶ አደሩን ማህበራዊ መሰረት እንዲቀይርና የአባላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሪፎርሙን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ፦ አቶ ሀብታሙ ካፍትን

Spread the love

በቤንች ሸኮ ዞን ግብርና ፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ የህብረት ስራ የንቅናቄ መድረክ በሚዛን አማን እየተካሄደ ይገኛል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት ህብረት ስራ ማህበራት ሰዎች የጋራ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ፣ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና መሰል ፍላጎቶችንና ችግሮችን ለመፍታትና ለማቅለል ሲሉ የሚመስርቱት ነው ብለዋል።

ያደጉና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ለዕድገታቸው ህብረት ስራ ማህበራትን መሰረት በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። በሀገራችን የህብረት ስራ አገልግሎት ከተጀመረ በርካታ አመታት የቆየ ሲሆን ከነ ውስንነቱም ቢሆን ለውጥ አምጥቷል ብለዋል። ህብረት ስራ ማህበራት በመሰረታዊነት የአርሶ አደሩን ማህበራዊ መሰረት የመቀየርና ወደ ሌላ ኢኮኖሚ የሚያሸጋግር ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁን እንጁ አሁን ባለው አደረጃጀት ፣ አወቃቀርና የአሰራር ስርዓት ዘርፉን ማዘመንና የህብረተሰቡን ለውጥ ማምጣት የሚችል ባለመሆኑ ሪፎርም አስፈልጓል ብለዋል። በቀጣይ ዘርፉን ለማሻገር አጠቃላይ ሪፎርሙን ወደ ስራ ማስገባትና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የዞኑ ግብርና ፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የህብረት ስራ ማህበራት የአርሶ አደሩን ብቻ ሳይሆን የንግዱ ማህበረሰብ የሚለወጥበት ተቋም ነው ብለዋል።

እንደ ዞን 456 ህብረት ስራ ማህበራት ፣ 4 ዩኒየን ፣ 142ሺ 919 የግለሰብ አባላት ፣ 432 ሚሊደን 829ሺ 766 ካፒታል በመያዝ በስራ ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ኃላፊው ባለፉት አመታት ከነ ጉድለቱም ቢሆን ለአርሶ አደሩ ለውጥ ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።

ህብረት ስራ ማህበራት በዋናነት ተወዳዳሪ ፣ በገበያ ውስጥ ተፈላጊ ፣ የሚታመኑ ፣ ለአባላት ተጠቃሚነት የሚሰሩ ፣ ጠንካራ የአባላት ተሳትፎ ያላቸው ፣ በውጤታማ የአመራርና ዘመናዊ አሰራር ፣ በስትራቴጂያዊ ዕቅድ እንዲመሩ እና አስተማማኝ ፋይናንስ ፣ ያደገ የዲጂታል ኢኮኖሚ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሪፎርሙ ማስፈለጉን ገልጸዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *