ሙስናን በመከላከሉ ሂደት ሁሉም ለውጤታማነቱ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ

Spread the love

“ወጣቶችን ያማከለ የጸረ _ሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል ” በሚል መሪ ቃል አለምአቀፍ የሙስና ቀን በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

በአለምአቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ፣በሀገራችን ለ20ኛ ጊዜ እንዲሁም በክልላችን ለ3ኛ ጊዜ በዓሉ በተለያዩ ሁነቶች በሚዛን አማን ከተማ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተከብሮ ውሏል።

በዓሉን በተመለከተም የውይይት ሰነድ ያቀረቡት በክልሉ የስነምግባር እና ጸረ _ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ታደሰ አይበራ የጸረ _ሙስና ትግሉ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ሁሉም ኃላፊነት በተሰማው መንገድ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

ሙስናን በብቃት ለመከላከል እንዲቻል መረጃዎችን በማደራጀትና በመተንተን የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል ።

በ2016 በጀት ዓመት ብቻ ኮሚሽኑ በሰራቸው የመከላከል ስራዎች ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ ከምዝበራ መታደግ መቻሉንም አቶ ታደሰ አይበራ ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍ አብራርተዋል ።

በመነሻ ጽሑፉ ዘርዘር ያሉ ሀሳቦች የተብራሩ ሲሆን ከመነሻ ጽሑፉ በመነሳትም ከተሳታፊዎች አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ቀርበዋል።

ሙስና ሊፈጸም የሚችለው በአስተሳሰብ በህሊናው የሰረቀ እንደሆነ ተሳታፊዎች አንስተዋል ።

ሙስናን ለመከላከል መንግስት ከተቋማት፣ከሀይማኖት አባቶች ጋር የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር አሰራሩን በማዘመን መስራት ይገባዋል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የምንበድለውና የምንሰርቀው የራሳችንን ወገን ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ሙስናን ለመከላከልም ከራስ በመጀመር ኃላፊነታችንን በተገቢው መወጣት አለብን ሲሉም ገልጸዋል።

የሙስና መከላከል ስራን በሚዲያ ከማስደገፍ አኳያ ከመደበኛ ዘገባ ውጭ በምርመራ ዘገባ መስራት ውጤታማ የሚያደርግ በመሆኑ ተገቢውን መረጃ ማደራጀትና ለጋዜጠኞች ተገቢውን የህግ ከለላ በመስጠት ሊሰራበት እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎች ጠይቀዋል።

በተሳታፊዎች በቀረቡ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ከኮሚሽኑ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል።

በክልሉ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የሙስናና ብልሹ አሰራር ዘርፍ ኃላፊና ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳግም ዳንኤል ሙስና ድንበር ተሻጋሪ አለምአቀፋዊ ወንጀል በመሆኑ በአንድነት ወጣቱን ማዕከል በማድረግ የመከላከል ስራውን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሙሉሰው ዘውዴ መድረኩን ባጠቃለሉበት ወቅት ሙስናን በመከላከሉ ሂደት ሁሉም ለውጤታማነቱ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል ።

እንደ ክልል የሙስና ተግባራትን ለመከላከል ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን የገለጹት ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ አድሏዊ አሰራሮችን፣ወገንተኝነትና ስልጣንን አለአግባብ መጠቀም ወንጀሎችን በተቀናጀ መንገድ የመከላከል ስራውን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ሙስናን መከላከል ሀገርን ማስቀጠል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ይህንን ተግባር ሁሉም በጋራ እንዲሰራ አሳስበዋል ።

በዕለቱ የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር የተደረገ ሲሆን ለአሸናፊዎች እና ለተወዳዳሪዎች የምስክር ወረቀት በመስጠት ፕሮግራሙ ተጠናቋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *