የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ዘላቂ ሠላምን በመገንባት ቀጣይነት ያለውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለመገንባት ያስችላል። አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር

Spread the love

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የባህልና ታሪክ ሲምፖዚየም በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

“ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለሀገራዊ መግባባት” በሚል መርህ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ አርባምንጭ ከተማ ህዳር 29 የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በማስመልከት በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህልና ታሪክ የሚያተኩር ሲምፖዚየም እየተካሄደ ይገኛል።

በጋሞ ባህልና ምርምር ማዕከል አዳራሽ ክቡራን የእለቱ እንግዶች በተገኙበት እየተካሄደ በሚገኘው ሲምፖዚየም ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፌ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገረ ባለፉት 18 ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የቀኑ መከበር ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ እሴቶቻቸውን በማጎልበት በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲወጡ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የዘንድሮው በዓል በሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መዋቅራዊ ሽግግር እየተተገበረ ባለበት ጊዜ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት አቶ አገኘሁ የበዓሉ መከበር የህዝቦችን የጋራ እሴቶችን በማስተዋወቅ፣ ዘላቂ ሠላምና ልማት ለማፋጠን የሚረዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፌ-ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፀሀይ ወራሶ በበኩላቸው ቀኑ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ማንነታቸውን፣ ታሪክና ባህላቸውን ለመላው አለም እንዲያስተዋውቁ ዕድል የፈጠረ መሆኑን በመግለጽ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በክልሉ መዘጋጀቱ የክልሉን የልማት አቅሞች ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ እንደሆነ ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በብዝሀነት ላይ የተመሠረተ የህብረብሄራዊነት መገለጫ መሆኑን የገለጹት አፌ-ጉባኤ ወ/ሮ ፀሀይ ይህንን አንድነት በጠንካራ መሠረት ላይ በመገንባት፣ አብሮነትና አንድነት እንዲሁም መቻቻልን አጠናከረው መቀጠል ይገባል ብለዋል።

“በዓሉን ስናከብር በለውጡ መንግሥት የመጡ ድሎችን ማስቀጠል ይገባል” ያሉ አፌ-ጉባኤ ወ/ሮ በህዝቦች መካከል ያለውን ሠላማዊ ግኑኝነት በማጠናከር ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለዘላቂ ሠላም መጎልበት መጠቀም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *