የሥራ ላይ ደህንነትንና የሰራተኞችን መብትና ጥቅም የማስከበር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል – ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል::

Spread the love

የኢንዱስትሪ ሰላምን የማረጋገጥ፣ ምርታማነትን የማሳደግ፣ የሥራ ላይ ደህንነትንና የሰራተኞችን ጥቅም የማስከበር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።

የዓለም የሠራተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለ49 ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ135 ጊዜ “ለሠላምና ለኑሮ ውድነት መፍትሔ እንሻለን” በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ ይገኛል።

በአዲስ አበባ በተከናወነው መርሃ ግብር የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የሰራተኛ ማህበራት ተወካዮችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የሰራተኞችን ጥቅምና መብቶች የማስከበር እንዲሁም ደህንነታቸውን የማስጠበቅ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የሰራተኛውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣ የሚነሱ ጥያቄዎችን በጥናት ላይ ተመስርቶ በሂደት ምላሽ ለመስጠትም አሰራሮች ተዘርግተው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢንዱስትሪ ሰላምን የማረጋገጥ፣ የሥራ ላይ ደህንነትንና የሰራተኞችን ጥቅም የማስከበር ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የሠራተኞችን መብትና ጥቅም በዘላቂነት ለማስጠበቅም አዳጊ ፍላጎቶችን መሠረት ያደረገ ሪፎርም ተሰርቶ ወደ ስራ የተገባ መሆኑንም ተናግረዋል።

በየደረጃው ያሉ ሰራተኞች የላቀ ብቃትና እውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸውም በመንግስት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ለሀገር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ማድረግም አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ካሣሁን ፎሎ፤ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር ከመንግሥት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ከማስከበር ባለፈ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ተቀምጠው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።

በየአመቱ ሚያዝያ 23 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን በዛሬው እለት በተለያዩ መርሃ ግብሮች በመከበር ላይ ይገኛል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *