


የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ከጎባ ክላስተር ኩታ ገጠም (ዞኖችና ወረዳዎች) ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ በአርብቶ አደር አካባቢዎች (በጎባ ክላስተር) ኩታ ገጠም ዞኖችና ወረዳዎች የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ የታቀደ ዕቅድ በክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ በአቶ ሀብታሙ አለሙ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ በተገቢው መደገፍና ለፀጥታ ሀይሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ማጠናከር፣ ባለድርሻ አካላት ተግባሩን በባለቤትነት ስሜት መምራት እንደሚገባቸው፣ ከአጎራባች ክልሎች ጋር በሚዋሰኑ አካባቢዎች የሚከሰተውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የጋራ የምክክር መድረክ በመፍጠር ቀጠናውን ሠላም ማደረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መስራት ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
የፀጥታ ችግር በአንድ ጊዜ ስራ ብቻ የማይፈታ ተያያዥነት ያለው ጉዳይ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ አቅዶ መስራት የሚጠይቅ መሆኑ በመድረኩ ተመልክቷል፡፡
የቀጠናውን ፀጥታ ለማስፈን ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ስራው ህዝባዊ መሰራት እንዲይዝ ማድረግና አካባቢዎቹን በመሠረተ ልማት ማስተሳሰር ተገቢ መሆኑን ያነሱት የመድረኩ ተሳታፊዎች ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ይህ መድረክ የፀጥታ ችግር መፍቻ መድረክ ብቻ ሳይሆን በህዝቦች መካከል ያለውን ጠንካራ ትስስር የሚናስቀጥልበት፣ በዚህም ልክ በኢኮኖሚ፣ በልማትና በጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ምክክር የሚደረግበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ በበኩላቸው ክልሉ ሲመሰረት የክልሉ መንግሥት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ የተነሳው በየጊዜው እየተነሣ ክልሉን የማልማት አቅም እየተፈታተነ ያለውን የፀጥታ ችግር መፍታት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም መነሻ ክልሉ ከተቋቋመ ወዲህ በተደረገው የፀጥታ ስራ አብዛኛዎቹ የፀጥታ ችግሮችን መፍታት ችለናል ያሉት አቶ ፋጂዮ ያሉንን ችግሮች በጋራ በመመካከር የክልሉን ሠላምና ፀጥታን በዘላቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በጎባ ክላስተር ኩታ ገጠም የኮንታ፣ የምዕራብ ኦሞ እና የካፋ ዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች ፣ የፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
