
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት መጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ ለ926 ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን አስታወቀ።
የክልሉ የይቅርታ ቦርድ በይቅርታ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ መሰረት መስፈርቱን የሚያሟሉ ታራሚዎችን ከመንግስት፣ ከህዝብና ከታራሚ ጥቅም አኳያ ሲመረምር መቆየቱን የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ እሸቱ ጎዴቶ ገልጸዋል ።
በተደረገው ምርመራም በአጠቃላይ የይቅርታ ጥያቄ ካቀረቡ 978 ታራሚዎች መካከል መስፈርቱን ያሟሉ 926 ታራሚዎች ጥያቄያቸው ለክልሉ መንግስት ቀርቦ የይቅርታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።
የይቅርታው ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል 920 ታራሚዎች ከእስር የሚለቀቁ ሲሆን÷ስድስቱ ደግሞ የእስራት ጊዜያቸው የተቀነሰላቸው መሆኑን አቶ እሸቱ ገልጸዋል።
ይቅርታ ከተደረገላቸው 926 ታራሚዎች ውስጥ 903 ወንዶች 23ቱ ሴቶች ሲሆኑ የይቅርታ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ከእስር የሚለቀቁ ታራሚዎች ለህብረተሰቡ የወንጀል ስጋት ሳይሆኑ የሰላም ሰባኪ፣ አምራችና ህግ አክባሪ ዜጋ ሆነው ህብረተሰቡን ሊቀላቀሉ እንደሚገባም አቶ እሸቱ ተናግረዋል ።
ታራሚዎቹ በማረሚያ ቤት በነበራቸው ቆይታ በአግባቡ ስለመታረማቸው፣ ስለመታነጻቸውና ስለመልካም ባህሪያቸው ምስክርነት የተሰጠባቸው መሆኑንም አመልክተዋል።
በታጠቅ አበበ
