የወሳኝ ኩነት ምዝገባን ውጤታማ ለማድረግ በየደረጃው ያለው አመራር ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ::

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዘርፍ በወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ድጋፋዊ ክትትል ግብረ መልስ ዙሪያ የባለድርሻ አካላት ምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄደ።

በክልሉ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ እንቅስቃሴን ዙሪያ ከክልሉ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በጥምረት የተዋቀረው የቴክኒክ ኮሚቴ በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች ያለው የምዝገባ ሂደት ላይ ባደረው የመስክ ምልከታ ግብረ መልስ አቅርቧል።

የቴክኒክ ኮሚቴው በዞኖችና ወረዳዎች ላይ ያለው የምዝገባ አፈጻጸም፣ የግብዓት ስርጭትና አጠቃቀም እንዲሁም የምዝገባ ስራውን ዲጂታይዝ ለማድረግ በተጀመረው እንቅስቃሴ ላይ ምልከታ ማድረጉ ተገልጿል።

በዚህም ከግብረ መልሱ መነሻ በየደረጃው ያለው አመራር በየአካባቢው የሚፈጠሩ የህዝብ መድረኮችን በመጠቀም ስለ ኩነቶች ምዝገባ ግንዛቤ መፍጠርና ተግባሩን በትኩረት መምራት እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በየደረጃው ያለው አመራር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ዘርፈ ብዙ ፋይዳን በጥልቀት በመረዳት ተግባሩን ተከታትሎ በመገምገም የሚገጥሙ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባው አሳስበዋል።

የምዝገባዉን ተግባር የበለጠ ዉጤታማ ለማድረግ በየደረጃው ካሉ የፐብሊክ ሰርቭስና የሰው ሀብት ልማት መዋቅሮች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ህብረተሰቡ ስለ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጠቀሜታ ተገንዝቦ ኩነቶች እንደተከሰቱ የማስመዝገብ ተግባርን በማህበረሰቡ ዉስጥ ባህል ማድረግ እንደሚጠበቅ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ደመቀ ጠቁመዋል።

ተልዕኮውን ለማሳካት ማነቆ የሆነውን የሰው ኃይል ክፍተት በማሟላትና የዘርፉ ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት ውጤታማ የኩነት ምዝገባ ስራ መስራት እንደሚገባ ያሳሰቡት ኃላፊው የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር አለበት ብለዋል።

አመራሩ ተግባሩን በባለቤትነት በመምራት የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት የክልሉ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ኃይል ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ አስራት አዳሮ የሰው ኃይል እጥረትን በምክንያታዊነት ተመርኩዞ የማሟላት ስራ በቀጣይ ይሰራል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ለወሳኝ ኩነት ምዝገባ ስራ የማይተካ ሚና የሚጫወቱ አካላት በመሆናቸው ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *