






ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ትኩረት በመስጠት ለመጪው ትውልድ የምትመች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በመረባረብ ይገባናል ሲሉ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።
”ምክር ቤቶቻችን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ አገር ግንባታ ስኬታችን” በሚል መሪ ሀሳብ የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች የስልጠና እና የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
በሰላም ሚኒስቴር በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት እንዲሁም የክልልና የከተማ መስተዳደር ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች ታድመዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብሄራዊ መግባባት በሚፈለገው ልክ መፍጠር ያልተቻለው ሁሉን ነገር ከትላንት ጋር ብቻ በማያያዝ ዛሬና ነገን በአግባቡ መመልከት ባለመቻሉ ነው።
ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ አገረ መንግስት ግንባታ ብሄራዊ መግባባት ወሳኝ ጉዳይ ቢሆንም ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር የተኬደባቸው መንገዶች ትክክለኛ አቅጣጫን የተከተሉ እንዳልነበሩ ገልጸዋል።
ይህም የምንመኘውንና የምንፈልገውን ብሄራዊ መግባባት መፍጠር እንዳንችል አድርጓል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የመንግስት ምስረታ ታሪክ ያላትና ቀደምት የስልጣኔ ባለቤት መሆኗን አስታውሰው የቅርብ ጊዜ የምስረታ ታሪክ ያላቸውና በሁለንተናዊ ዕድገት ከኢትዮጵያ የቀደሙ አገሮች ዋነኛ ምስጢር ከትናንት ታሪካቸው ተምረው ነጋቸውን የሚያሳምር ስራ መስራት መሆኑን ገልጸዋል።
ሁሉን ነገር ከትላንት ጋር ብቻ በማያያዝና ትላንት ላይ ተቸክሎ በመቆየት ለውጥ እንደማይመጣ ገልጸው ዛሬና ነገን በማሰብ በጋራ መትጋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ዘላቂ ሰላምና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ነገን መናፈቅና ለነገ የተሻለ መመኘት ወሳኝ መሆኑንም ነው ያብራሩት።
ዛሬ ላይ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች መግባባት በመፍጠር ነገ የምንመኛትን አገር እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ለዚህም ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን በመተው የጋራ ትርክቶች ላይ በማተኮር ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሁላችንም በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ትኩረት በመስጠት ለመጪው ትውልድ የምትመች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር መግባባት ላይ ለመድረስ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ለኮሚሽኑ ውጤታማነት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያዊያን በአብሮነትና በመከባበር ለትውልድ የሚሻገር መልካም ስራ መስራት ይገባናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የብዝሃ ብሄሮች አገር እንደመሆኗ የሁሉንም ማንነት በእኩል ደረጃ መቀበል ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፀሀይ ወራሳ እንደ አገር ያለውን ብዝሃነት ተቀብሎ የጋራ እሴቶች ላይ መስራትና የህዝቦችን አንድነት ማጠናከር ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ቁልፍ መንገድ መሆኑን አንስተዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋጤ ስርሞሎ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የሁሉም ሃላፊነት ቢሆንም በተለይ አስፈጻሚ አካላት የሰላም ጉዳይ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ የምክር ቤት አባላት የሚያደርጉትን ክትትልና ቁጥጥር ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ነው ያነሱት ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
