



ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ የልማት ጉዞ በርካታ ተግባራትን በቁርጠኝነት በማከናወን ላይ እንደምትገኝ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ሳሙኤል ዶ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አመታት በአረንጓዴ ልማት ያስመዘገበችው ውጤት አስደናቂ እና ለሌሎች ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው፡፡
“ኢትዮጵያ አረንጓዴ ጉዞ 2030” በሚል መሪ ሃሳብ አመታዊ የልማት ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በኮንፈረንሱ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ፤ የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍሰሃጽዮንን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት በርካታ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን የጠቀሱት ሳሙኤል ዶ፥ በያዘችው የልማት እቅድ የአየር ንብረትንና አረንጓዴ ልማትን አጣምራ እየሰራች እንደምትገኝ አንስተዋል።
አለምን እያሰጋ የሚገኘውና በፍጥነት እየተለወጠ የመጣው የአየር ንብረት ቀውስ በምድራችን ከፍተኛ ስጋት እያስከተለ ይገኛል ብለዋል፡፡
ይህን የአየር ንብረት ስጋት በመገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ ፣በትብብር በመስራት አፋጣኝና ወሳኝ እርምጃ መውሰድ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
በመሆኑም ችግሩን ለመከላከል ውጤታማ ስራ እየሰሩ የሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራትን ማገዝና መደገፍ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ የልማት ጉዞ በርካታ ተግባራትን በቁርጠኝነት በማከናወን ላይ እንደምትገኝ አንስተዋል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም 40 ቢሊየን ችግኝ መትከሏን በማድነቅ የፓሪስ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ያሳየችውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የምታከናውናቸው በርካታ ተግባራት የተፈጥሮ ሃብቶቿን ለመጠበቅ የወሰደችውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡
በዚህም ታዳሽ ሃይልን በተመጣጣኝ ዋጋ ለጎረቤት አገራት ለማቅረብ ከፍተኛ ስራ እየሰራች መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ለምትሰራው ስራ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት በማስታወቅ በዚህ ረገድ የግል ሴክተሩ አጋርነት በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የፕላንና ልማት ሚንስትር ዴኤታ በረከት ፍስሃጽዮን በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በርካታ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ አስታውቀዋል።
በዚህም እኤአ በ2030 አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ እየሰራች እንደምትገኝ በመጥቀስ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ በካይ ጋዝን ለመቀነስ አበክራ እየሰራች ነው ብለዋል፡፡
በዚህም ለአየር ንብረት ለውጥ የሚጋልጡ ሴክተሮችን በመለየት ብሄራዊ አዳፕቴሽን ፕላንን ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ኢኮኖሚ መገንባት የሚያስችላትን ስትራቴጂ በመንደፍ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ 40 ቢሊየን ችግኞች መትከሏን በመጥቀስ ተግባሩ የአገሪቱን የደን ሃብት ሽፋን እኤአ በ2019 ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ እኤአ በ2023 ወደ 23 ነጥብ 6 ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል፡፡
የአየር ንብረትን መሰረት አድርጎ በተተገበረው የስንዴ ልማት ከውጭ የምታስገባውን ምርት በማስቀረት ወደ ውጭ መላክ መጀመሯን አስረድተዋል፡፡
እንዲሁም አረንጓዴ ትራንስፖርትን ተግባራዊ በማድረግ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ በካይ ጋዞችን መቀነስ መቻሏን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የተለያዩ ፖሊሲዎችን በመንደፍ በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝና በቀጣይም ተግባሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል በመድረኩ ተገልጿል ያለው ኢዜአ ነው፡፡
