















ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት በዚህ አምድ አጠቃላይ የክልላችንን ገጽታ፣ የምዕራብ ኦሞ፣ የካፋና የዳዉሮ ዞኖችን አጠቃላይ ገጽታ የሚያሳዩ ጽሁፎችን እንደየቅደምተከተላቸው ለውድ አንባቢዎቻችን አድርሰናል፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ ከክልላችን ዞኖች አንዱ የሆነውን የቤንች ሸኮ ዞንን እንቃኛለን፡፡ መልካም ንባብ!
የቤንች ሸኮ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት ከተዋቀሩ ስድስት ዞኖች አንዱ ነዉ፡፡ ዞኑ በስድስት ወረዳዎች፣ በአራት ከተማ አስተዳደሮች፣ በ137 ቀበሌዎች (123 የገጠርና 14 የከተማ ቀበሌዎች) የተደራጀ ነዉ፡፡ ዞኑ በስተደቡብና ደቡብ ምዕራብ ከምዕራብ ኦሞ ዞን፣ በስተምዕራብ ከጋምቤላ ክልል፣ በስተሰሜን ከሸካ ዞን እና በስተምስራቅ ከካፋ ዞን ጋር ይዋሰናል።
የዞኑ ዋና ከተማ ሚዛን አማን ሱሆን ከተማው ከክልሉ ብዝሃ ዋና ከተሞች አንዱ ነው፡፡ ሚዛን አማን ከአዲስ አበባ 568 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን ከክልሉ የአስተዳደርና ፖለቲካ መቀመጫ ቦንጋ ከተማ ደግሞ በ123 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በስተ ምዕራብ ይገኛል፡፡ ከተማዋ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ተፈቃቅረዉና ተከባብረዉ በአንድነት የሚኖሩባት ከተማ በመሆና ትንሿ ኢትዮጵያ ያስብላታል፡፡
በዞኑ ያሉ ነባር ብሔረሰቦች ቤንችና ሸኮ ሲሆኑ እንደቅደምተከተላቸው በኦሞአዊ የቤንችኛ እና የሸኮኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው፡፡ እነዚህ ቋንቋዎች የቋንቋ ቤተሰብ የሚመደቡ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በርካታ የኢትዮጵያ ብሔር/ ብሔረሰቦች ከእነዚህ ነባር ብሔረሰቦች ጋር ተጋብተውና ተጋምደው በሠላም፣ በፍቅር፣ በመከባበርና በመደጋገፍ የሚኖሩበት ዞን ነው የቤንች ሸኮ ዞን፡፡
የዞኑ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 534 ሺህ 600 ሄክታር መሬት ይሸፍናል። የአየር ንብረቱ ደጋ 56.54 % ፣ ወይና ደጋ 15.44 % እና ቆላ ደግሞ 28.02 % ነዉ፡፡ በመሆኑም የቤንች ሸኮ ዞን ለቡናና ቅመማቅመም፣ ለሰብል ልማት፣ ለእንስሳት እርባታና ለኢንዱስትሪ ተከላ ተስማሚ የአየር ንብረትና ፍጹም ሠላም የሰፈነበት ነዉ፡፡
በዞኑ የተለያዩ ሰብሎች እንደ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ገብስ ወዘተ በስፋት ይመረታል። ከፍራፍሬ ረገድም ሙዝ፣ ማንጎ፣ አቦካዶ፣ ብርትኳን ጭምር የዞኑ ሌላኛው ገጽታ ነው። እንሰትና እንደ ጎደሬና ኬቺ ያሉ የሥራሥር ምርቶችም በዞኑ በስፋት ይመረታሉ፡፡
ዞኑ ቡና በጥራትና በብዛት በማምረት የሚታወቅ ሲሆን ለሀገራችን በዘርፉ የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል። ከቅመማ ቅመምም ዝንጅብል፣ እርድ፣ ቁንዶ በርበሬ እና ኮሮሪማ በብዛት እና በጥራት ተመርተው ለማዕከላዊና ለውጭ ገበያ በማቅረብ አንጻር ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል የቤንች ሸኮ ዞን።
ከመሬት አጠቃቀም ረገድ በዞኑ በዓመታዊ ሰብል የተያዘ 144 ሺህ 612 እና በቋሚ ሰብሎች የተያዘ 158 ሺህ 672 በድምሩ 303 ሺህ 285 ሄክታር መሬት በቋሚ እና ዓመታዊ ሰብሎች መሸፈን ተችሏል።
የግጦሽ መሬት 1 ሺህ 559 ሄክታር ፣ በደን የተሸፈነ በአጠቃላይ 179 ሺህ 647 ሄክታር፣ በውሃ የተሸፈነ 4 ሺህ 59 እና በሌሎች የተያዘ 25 ሺህ 579 ሲሆን ወደፊት ሊታረስ ወይም ሊለማ የሚችል መሬት 18 ሺህ 326 ሄክታር ነው።
ከጤና ተቋማት አኳ ዞኑ አንድ ማስተማሪያ ሆስፒታል፣ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ 26 ጤና ጣቢያዎች እና 114 ጤና ኬላዎች በመንግስት ተሰርተዉ የጤና አገልግሎቱን ጥራት እና ተደራሽነት ላይ የበኩላቸዉን ሚና እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል በግሉ ዘርፍ አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና 6 ክሊንኮች ወደ ህብረተሰቡ ተደራሽ በመሆን አገልግሎት እየሰጡ ናቸዉ፡፡
ከትምህርት ተቋማት አንፃር በዞኑ 246 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣31 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አኳያ የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ፣ አማን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ የሚዛን ግብርና ኮሌጅ በተጨማሪ 4 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ይገኛሉ፡፡
ከመሠረተ ልማት አንጻር ዞኑ በፌዴራልና ዞን መንግስት ተሰርተዉ አገልግሎት እየሰጡ ያለዉ የአስፋልት መንገድ 111 ኪሎ ሜትር ፣ የፌዴራል ጠጠር መንገድ 30 ነጥብ 19 ኪሎሜትር ፣ ክልላዊ የገጠር መንገድ 132 ኪሎሜትር ፣ የቀበሌ ተደራሽ መንገድ /የዩራፕ/ 421 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ጥርጊያ መንገድ 128 ነጥብ 77 ኪሎ ሜትር ሲሆን በጠቅላላ 863 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር መንገድ ተሰርቶ የትራንስፖርት ዘርፉን እያሳለጠ ይገኛል፡፡
የቤንች ሸኮ ዞን ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት የሚሆኑ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስህቦች ባለቤት ነው፡፡ የገበታ ለትውልድ አካል የሆነውና በደንቢ ሰው ሠራሽ ሀይቅ ላይ እየተገነባ ያለው የደንቢ ሎጅና የሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፍያን ጨምሮ በርካታ ፏፏቴዎች፣ ዋሻዎችና ሌሎች የቱርስት መሲህቦች በዞኑ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ በዞኗ የሚገኙ የነባር ብሔረሰቦች ያልተነካና ያልተበረዙ ትውፊቶች ፣ ቱባ ባህሎች ዛሬም ድረስ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን ቀልብ እንዳሰቡ መዝለቅ ችለዋል፡፡
በቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ረገድ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ግንባታ እንዲሁም ለኢኮ ቱሪዝም፣ ለአግሮ ቱሪዝምና ለመሳሰሉት ኢንቨስትመንቶች ላይ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች የተመቻቸ የቱሪዝም ኢንቬስትመንት አቅም ያለው ዞን ነው፡፡
በተለይም ዞኑ በመልካም አስተዳደርና በተረጋጋ የፖለቲካ ስርአት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋትና በተደራሽነቱ እያደገ የሚገኝ መሰረተ ልማት፣ ሰፊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የሚደረግበት ከመሆኑም በላይ አሁን ላይ የኢንቨስትመንትና የኮንፍረንስ ቱሪዚም መዳረሻ የሆነ ዞን ነው፡፡
ከላይ በተጠቀሱትና በሌሎች ምክንያት የዞኑ የቱሪስት ፍሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ወደ አካባቢው የሚመጡ ጎቢኝዎችን ፍላጎት ለማሟላት ደረጃውን የጠበቀ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በጥራትና በብዛት በመገንባት ላይ የሚገኝ ዞን ነው፡፡ ይህም በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ፣ የውጭ ምንዛሪን ለማስገኘትና የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በማስፋፋቱ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ እየተጫወተም ይገኛል፡፡
