




ከዓመታት አዙሪት መውጣት ያልቻልነው ችግሮቻችንን በውይይት መፍታት ባለመቻላችን ነው ሲሉ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፌደራል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ንግግር ያደረጉት ፕሮፌሰር መስፍን፣ የእድሜ ጠገብ ባለታሪክ የሆነችው ኢትዮጵያ በብዙ ውጣውረድ ውስጥ ማለፏን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ የገጠሟን ችግሮች ለመፍታት ህዝቡን በማሳተፍ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን ኮሚሽኑ በርካታ ስራዎችን መስራቱን አንስተዋል፡፡
አጀንዳ ከማሰባሰብ አኳያ የትግራይ ክልልን በምክክር ሂደቱ እንዲካተት ማድረግ እና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አጀንዳዎችን ማሰባሰብ ቀሪ ስራዎች ስለመሆናቸው ገልጸዋል፡፡
በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሂደቱ እየተሳተፉ ቢሆንም የተወሰኑ ፓርቲዎች የዚህ ታሪካዊ ሂደት አካል አይደሉም ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ በመሆኑም በሂደቱ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፌዴራል ተቋማት ተወካዮች፣ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ የመከላከያ ሠራዊት እና ፌዴራል ፖሊስ ተወካዮች፣ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ተወካዮች፣ የሴቶች ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ተወካዮች፣ የመገናኛ ብዙኀን ተወካዮች፣ የማኅበራት ተወካዮች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ከፍሎች ተገኝተዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
