




በክልሉ ግብርና ቢሮ የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ከናቡ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በቡና ልማትና ምርት አቅርቦት አፈጻጸም እና በአዲሱ የአውሮፓ ዩኒየን ደንብ(EUDR) ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የክልሉን ኢኮኖሚ ከሚመሩት ሰብሎች ግንባር ቀደሙ ቡና መሆኑን ገልጸዋል ።
ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ በተሰራው ስራ ከ60 ሺህ በላይ ሄክታር ማሳ በቡና መሸፈኑን ተናግረዋል ።
በዚህም በክልሉ ከ580 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በቡና መሸፈኑን እና የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደተቻለ አንስተዋል።
ቡና የሀገር ሀብት የውጭ ምንዛሪ የሚያሰገኝ እንደመሆኑ መጠን በግብይት ሂደት በህግ ሊመራ ይገባዋል ሲሉም ተናግረዋል ።
በክልሉ እስካሁን በአማካይ 54 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል ።
በዘንድሮው 2017 በጀት ዓመት በ11 ወራት ውስጥ ከ43 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡንም አቶ ማስረሻ ተናግረዋል ።
በዓመት በክልሉ ከ230_240 ሺህ ቶን ቡና እንደሚመረት ያስታወሱት አቶ ማስረሻ ለማዕከላዊ ገበያ ከማቅረብ አኳያ ያለው መሠረታዊ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ለውጤታማነቱ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት የደን ልማቶችን ጠብቆ በሚመረቱ ምርቶች አርሶአደሮች እና አልሚ ባለሀብቱ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ባወጣው ደንብ አስቻይ ሁኔታዎችን በማለፍ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን እና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በደንቡ ላይ ግልጽነት በመፍጠር ወደ ስራ መግባት ይገባናልም ብለዋል።
ክልሉ በቅመማ ቅመምና ሻይ ልማት ሰብሎች ክልላዊ ኢኒሼቲቮችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ ሲሆን በዚህ ዘርፍ አልሚ ባለሀብቱና አርሶአደሮች የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም አሳስበዋል ።
የክልሉ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ ባለፉት 11 ወራት የተከናወኑ የአፈጻጸም ሪፖርት ለውይይት አቅርበዋል።
ባለፉት በበጀት ዓመቱ 71 ሺህ 291 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ 43 ሺ 321 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡንና ከዕቅድ አኳያ 60 ከመቶ ላይ መሆኑ መሠረታዊ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ባለድርሻ አካላት ትኩረት እንዲሰጡበትም ጠይቀዋል።
በናቡ ኢትዮጵያ የቦንጋ ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ አሳየ አለማየሁ ከአውሮፓ ህብረት ከወጣው ደንብ ጋር ተያይዞ አርሶአደሮችና አልሚ ባለሀብቶች ከሚያመርቱት ምርት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ በሚሆኑበት ጉዳይ ዙሪያ ሰነድ አቅርበዋል ።
ደንን ከውድመት በመጠበቅ በደን ውስጥ ከሚመረቱ ምርቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለመሆን የወጣው የአውሮፓ ህብረት ደንብ እንደሚደነግግና ደንቡን መከተል የሚያስገኘውን ጥቅም አቶ አሳየ አብራርተዋል ።
በታጠቅ አበበ
