




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የኮ-ዋሽ (COWASH)ፕሮግራም አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ የክልሉ የኮ-ዋሽ ስትሪንግ ኮሚቴ የ2017 በጀት አመት የኮዋሽ ፕሮግራም የ10 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ምክክር ያደረገ ሲሆን የ2018 በጀት አመት የፕሮግራሙን ዕቅድ በገምግሞ 50 ሚሊዮን 106 ሺህ 479 ብር በጀት አፅድቋል።
በጀቱ 21 ሚሊዮን 237 ሺህ 323 ብር ከፊላንድ መንግስት ድጋፍ እና 28 ሚሊዮን 869 ሺህ 156 ብር ከኢትዮጵያ መንግስት በተገኘ ገንዘብ የሚሰራ ስለመሆኑም ተመላክቷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውሃ ፣ ማእድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው በክልሉ የመጠጥ ውሃ እና ሳንቴሽን አገልግሎት ተደራሽነት በጣም ውስን በመሆኑ የኮ-ዋሽ ፕሮግራም ለክልላችን በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኮዋሽ ፕሮግራም የማህበረሰብ ተሳትፎን መርህ በማድረግ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና በሀይጂን ላይ የሚሰራ መሆኑን ገልፀው ፕሮግራሙ የሚተገበረው በኢትዮጵያ እና ፊንላንድ መንግሥት በሁለትዮሽ ትብብር መሆኑን ጠቁመዋል።
የኮዋሽ ፕሮግራም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ በርካታ ውጤታማ ሥራ እየሰራ መሆኑንና በትምህርት ፣ በጤና ፣ በሴቶችና ህፃናትና እና በዉሃ እንዲሁም በፋይናንስ ሴክተሮች የጋራ ቅንጅት የሚተገበር መሆኑን ጠቅሰዋል።
የፕሮግራሙ በክልሉ በዳውሮ ዞን በሁለት ወረደዎች ማለትም በማሪ ማንሳ እና በከጪ ወረዳዎች ለህብረተከቡ በት/ቤቶች ፣በጤና ተቋማት የንጹህ መጠጥ ውሃ እና የመጸዳጃ አገልግሎት ፍላጎትን ተደራሽ ለማድረግ መንግስት ከህብረተሰቡ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል።
በምክክር መድረኩ የፕሮግራሙ በእስካሁኑ አፈጻጸም የተመዘገቡ እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ጨምሮ የ2018 በጀት አመት ዕቅድ በክልሉ ኮ-ዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪ በኢንጂነር ገሠሠ ገበየሁ ቀርቦ በመድረኩ ተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።
ባለፉት 11 ወራት ውስጥ 20 የማህበረሰብ ውሃ ተቋማት፣ በትምህርት ቤት 1 የመፀዳጃ ቤት፣ 4 የሴቶች የመፀዳጃ ቤቶች፣ 1 የጤና ውሃ ተቋማትና 2 መፀዳጃ ቤቶች በፕሮግራሙ መገንባታቸው ፕሮግራም አስተባባሪ በሪፖርቱ ተመልክቷል።
በፕሮግራሙ የሚተገበሩ ተግባራት በቀጣይ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የቅርብ ክትትል የሚደረግ ስለመሆኑ ተመላክቷል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
