




ክልላዊ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዞኑ ታርጫ ከተማ ተደርጓል።
በዚህ ዘመቻ በክልሉ ሁሉም ቀበሌያት የተቀናጀ 2ኛ ዙር የልጅነት ልምሻ በሽታ መከላከያ ክትባት ከግንቦት 22-25/2017 ዓ.ም እንደሚሰጥም ተገልጿል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ቦጋለ እንደገለፁት ይህ የልጅነት ልምሻ በሽታ በብዛት ከሰሃራ በታች ባሉት አገራት የሚታይ በሽታ በመሆኑ በአገር ደረጃ በሽታውን ለማጥፋት በሚቻልበት ሂደት ላይ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በሽታውን ለመከላከል እንዲቻል ክትባት ብቻ መስጠት ሳይሆን በተበከለ ውኃና ምግብ የሚተላለፍ በሽታ በመሆኑ የአካባቢንና የግል ንጽሕና በመጠበቅ መከላከል እንደሚቻልም ትኩረት ተደርጎ ሊሠራ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ከዘመቻው ጎን ለጎን በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕጻናትና እናቶችንም የመለየት ሥራ ይሠራልም ብለዋል።
በክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የዕለቱ የቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ ሙሉቀን አሰፋ እንደገለፁት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠዉን የልጅነት ልምሻ በሽታ በሀገሪቱ ከተመረጡ 10 ክልሎች መከካል አንዱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሲሆን በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ቀበሌያት ተደራሽ ይደረጋል።
በዚህ የክትባት ዘመቻም 564 ሺህ 624 እድሜያቸዉ ከ5 ዓመት በታች የሚሆኑ ልጆች የሚከተቡ ይሆናሉ ብለዋል።
ከእነዚህም መካከል በዳዉሮ ዞን ብቻ ከ1 መቶ 18 ሺህ በላይ ሕጻናት የሚከተቡ እንደሆነም ገልጸዋል።
የ1ኛ ዙር የተቀናጀ የክትባት ዘመቻ ላይ ከመቶ እጅ በላይ ማሣካት መቻሉንም በመጠቆም የሁለተኛ ዙር የተቀናጀ የልጅነት ልምሻ ክትባት በታቀደ ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በዚህ በተቀናጀ የክትባት ዘመቻ ኤም ፖክስ (M_Pox) በሽታ ግንዛቤ የመፍጠር እና የአሰሳ ስራ፥ በኩፍኝ ክትባት ዘመቻ ወቅት የተለዩ የተወሳሰበ የስርዓተ ምግብ ችግር ያለባቸዉን ልጆችና እናቶችን የመለየት ሥራም ትኩረት እንደሚደረግም ነው የገለጹት ።
በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላተስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ክትባቱን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት በአገር ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጡ ክትባቶች ጤናማ ትውልድን በመገንባት የብልጽግና ጉዞን ለማረጋገጥ ያስችላሉ።
ስለዚህ ጤንነቱ የተጠበቀ ትውልድ ለማፍራት እንዲቻል የሚሰጡ ክትባቶች የተሳኩ እንዲሆኑ ለማስቻል ሁሉም የባለድርሻዎች በተቀናጀ ርብርብ ሊሠሩ ይገባልም ብለዋል።
ማኅበረሰቡም በዘላቂነት የልጅነት ልምሻ በሽታን ማጥፋት እንዲችል ሀገሪቱ የተለያዩ ኢንሸቲቮችን ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች በመሆኑ የግልና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
አሁን ላይ ቤት ለቤት በሚደረገውና በተመረጡ የመዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤቶች የክትባት ዘመቻ በተሟላ ሁኔታ ጤናን ለማስጠበቅ እንዲችል እንዲሁም እድሜያቸው ከ1 አመት በላይ ሆነዉ ክትባት ያልጀመሩና ጀምረዉ ያቋረጡ ልጆች ክትባት እንዲጀምሩ ለማድረግ የልየታ ሥራም እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ቆልማማ እግር ችግር ያለባቸዉን ልጆች ልየታ፣ የፊስቱላ ችግር ያለባቸው እናቶች ልየታ በዘመቻዉ ላይ በተሰማሩ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ይደረጋልም ብለዋል።
በዘመቻውም የልጅነት ልምሻ ምልክት ያለባቸው ሕጻናትና ከወሊድ ጋር በተያይዘ የሽንትና የሰገራ መቆጣጠር ችግር የገጠማቸው ሴቶች በመለየት ወደ ሕክምና ተቋም እንዲሄዱ የማድረግ ሥራም እንደሚሠራም ተገልጿል።
በማስጀመሪያው መርሃ ግብር በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላተስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ፣ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ፀሐይ ደርጫን ጨምሮ የክልሉ ጤና ቢሮና የዞን ጤና መምሪያ የማኔጅመንት አባላት እንዲሁም ሌሎችም የባለድርሻ አካላት በታርጫ አድቬንቲስት ትምህርት ቤት ተገኝተው ማስጀመራቻዉን ዋካ ኤፍ ዘግቧል።
