የክልሉ ትምህርት ቢሮ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በክልሉ በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ሰፊ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

Spread the love

በክልሉ የኮንታ ዞን በማህበረሰብና በመንግስት ተሳትፎ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ በኮንትኛ ቋንቋ ያሳተመውን ከ64 ሺ በላይ ከቅድመ 1ኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል የመማሪያና የማስተማሪያ መፅሀፍት ርክክብ ተደርጓል።

በመድረኩ የተገኙ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ አዲሱ ስርዓተ ትምህርት በክልሉ በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ሰፊ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ የቢሮው ምክትል ሀላፊና ስርዓተ ትምህርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ደረሰ ገቲሳ ገልጸዋል።

የመፅሀፍት ህትመቱ እንደ ሀገር በትምህርት ዘርፍ ያጋጠመውን ስብራት እንደሚጠገን ያብራሩ የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነጋ አበራ በዞኑ የትምህርት ጥራትን ለማረጋጉጥ በተከናወኑ በርካታ ስራዎች ውጤት እየተመዘገበ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኮንታ ዞን በተለይ ከቅድመ መደበኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያሉ የመማሪያ መፅሀፍት በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲታተም በተቀመጠው መሠረት ዞኑ መላውን የዞኑን ህዝብ በማስተባበር የመማሪያ መፅሀፍትን በአፍ መፍቻ ቋንቋ አሳትሞ በማሰራጨት ግንባር ቀደም ተግባር አከናውኗልም ብለዋል።

አቶ ነጋ አበራ አክለውም በዞኑ በእውቀት የዳበረና ተወዳዳሪ ትውልድ እንዲፈጠር ከመደበኛ ትምህርት ቤት በተጨማሪ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤት ተከፍቶ 50 የሚሆኑ ተማሪዎች እየተማሩ እንደሚኝም አብራርተዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የዞኑ ህዝብ የዞኑን አስተዳደርና እንደ ሀገር የተቀመጠውን የትምህርት ለትውልድ ጥሪ ተቀብለው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ10 ሚልዮን ብር በላይ በማዋጣት መፅሀፍት እንዲታትሙ ስላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸውን ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሀገርን ማዳን ከትምህርት ስብራት ጥገና ስራ የሚጀመር ስለሆነ በዞኑ በትምህርት ዘርፍ የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት የኮንታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ገዛኸኝ ገዝሙ ናቸው።

መፅሀፍት ማሳተም ብቻውን ለትምህርት ዘርፍ ስብራት መፍትሔ አይሆንም ያሉት ዋና አስተዳዳሪ በዞኑ የትምህርት ዘርፍ ስብራትን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት መላው የዞኑ ህብረተሰብ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የታተሙ መፅሀፍት ወደ ትምህርት ቤቶች ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆንና የሚጠበቅ ውጤት እንዲመጣ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ መልዕክት ተላልፏል ሲል ደሬቴድ ዋካ ቅርንጫፍ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *