የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የወጣቶች ምክር ቤት ተመሰረተ::

Spread the love

ዛሬ በተደረገዉ ምክር ቤት ምስረታ 13 ሥራ አስፈጻሚና 42 የምክር ቤት አባላት ተመርጠዋል።

ምክር ቤቱ ወጣት ይስሃቅ ንጉሴን የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ና ወጣት ትህትና ቆጭቶን ምክትል ሰብሳቢ በማድረግ መርጠዋል።

በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ፡ ገናና የሆነ ሀገር የትክክለኛ ትርክት ውጤት ስለሆነ ብሔራዊነት ገዥ ትርክታችን ሆኖ እንዲገነባ ወጣቱ ፅንፍ ከረገጡ አስተሳሰቦች ራሱን በመጠበቅ ገዥ ትርክቱ ጎልቶ እንዲወጣ ባለቤት ሆኖ መስራት እንደሚኖርበት አፅንኦት ሰጥተዋል።

አክለውም በምክንያታዊነትና በሀሳብ የሚያምን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያስጠብቅ ወጣት በማነፅ በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

መንግስት የወጣቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በገጠርም ሆነ በከተማ በስራ ዕድል ፈጠራ በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም በወጣቱም በኩል ከስራ ፈላጊነት ይልቅ የስራ ፈጠራ ሀሳቦች ጎልተው መውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በተጨማሪም የሰላም ዕጦት ግንባር ቀደም ሰለባ ወጣቱ በመሆኑ ሰላሙን በትኩረት መጠበቅ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ዛሬ ምስረታዉን የተደረገዉ የወጣቶች ምክር ቤት ጠንካራ ተቋም ሆኖ ሀሳብ የነገሰበት፣ ክርክር የሚበረታበትና ምክንያታዊነትና ሚዛናዊነት ጎልቶ የሚወጣበት ተቋም እንዲሆን በብርቱ እንዲትሰሩ ስሉ አቶ አልማዉ ጥሪዉን አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ሙና አህመድ ህገ- መንግስቱንና ፖሊሲውን መሰረት በማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ የወጣት አደረጃጀቶች ተቋቁመው የተለያዩ ተግባራት ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ሆኖም እንደሀገር በመንግስትና በወጣቶች መካከል ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል፥ በወጣቶች የሚመራና ከመንግስት ጋር በመመካከር የሚሰራ እውነተኛ የወጣቶች ድምፅ የሚሆን ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ገነት መኩሪያ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶች ምክር ቤት በይፋ በመቋቋሙ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በክልሉ የወጣቶች ምክር ቤት እንዲቋቋም መደረጉም በተለይም የክልሉን ወጣቶች ድምፅ ለመስማት፥ ፍትሃዊ አሰራሮችን ለመዘርጋትና ተጠቃሚነትን ለማስፈን በአጠቃላይም በወጣቶች ህይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማሳካት የላቀ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል።

የክልሉ የወጣቶች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆኖ የተመረጠው ወጣት ይስሃቅ ንጉሴ በበኩሉ በመመረጡ የተሰማውን ደስታ ገልጾ የወጣቶችን መብትና ጥቅማጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ከመንግስትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የተመረጡ የምክር ቤት አባላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በከፍተኛ ተነሳሽነትና በቅንጅት እንደሚሰሩ በኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወጣት ፉአድ ገና አማካኝነት ቃለ-መሃላ ፈፅመዋል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚዎች፥ የሃይማኖት ተወካዮች፥ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች፥ የፌደራል የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች ከየመዋቅሩ የተውጣጡ የወጣት አደረጃጀት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

በእንዳላማዉ ጌታ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *