







የግብርና ሚኒስቴር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈፃሚ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ስርዓተ-ፆታና ኤች አይ ቪ ኤድስ ሜንስትሪምንግ ጋር በመቀናጀት ለክልሉ ግብርና ቢሮ የስራ ኃላፊዎች፤ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶችና ፕሮግራሞች በስርዓተ-ፆታና ማህበራዊ ጉዳይ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ዙሪያ የተዘጋጀዉ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የዉይይት መድረኩ ዋነኛ ዓላማ በሥርዓተ-ፆታና ማህበራዊ ጉዳዮች አካቶ ትግበራ ዙሪያ በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ልዩ አመካሪና የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሀንስ መላኩ፣ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በግብርናው ዘርፍ የሴቶችና አካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በዘርፉ ምርታማነትን በማሳደግ ድህነትን ለማሸነፍ የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሴቶችና አካል ጉዳተኞችን በግብርናውን ዘርፍ በማሳተፍና በቀጣይነት ድጋፍ በማድረግ ተጠቃሚ ማድረግ የሁሉንም አካላት ድጋፍ የሚሻ መሆኑን ጠቅሰዉ በሁሉም የልማት ዕድገት ሁሉንም ዜጋ በማሳተፍ የሀገራችንን ብልጸግና ማረጋገጥ አለብን በማለትም ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ስርዓተ-ፆታና ኤች አይቪ ሜንስትምንግ ባለሙያ ወ/ሮ ሮዛ ቃሲምወ/ሮ ሮዛ ቃሲም የክልላችን መንግሥት ለዚህ ዘርፍ ሰፊ ትኩረት በመስጠት በሁሉም የሥራ ዘርፎች ዉስጥ በማካተት፣ በማቀናጀትና በመደገፍና ክትትል በማድረግ ሞዴል ሴት አርሶ አደሮችን መፍጠርና ማብቃት እንዲሁም ለሴት አርሶ አደሮች የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችን የመደገፍ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
አክለዉም፣ ከዞን እስከ ወረዳ ድረስ ባሉ መዋቅሮች የሠዉ ኃይል አደረጃጀት ያለመሟላት ተግባራትን በባለቤትነት አቅዶ ሥራዎችን ለቅሞ ለማሳካት የተደራጀ ሰንሰለት የሌለዉ መሆኑ በሚፈለገዉ ልክ ዉጤት ማስመዝገብ እንዳልተቻለ ጠቅሰዉ የዛሬዉ መድረክ ይህንን ችግር ለመፍታት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ እንደሚረዳም አስረድተዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ገነት አብደላ ባደረጉት ንግግር በሁሉም የልማት ዘርፎች ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሴቶችን የልማት ተሳታፊና እኩል ተጠቃሚ ማድረግ የሰብዓአዊ መብት ማረጋገጥ እና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መደገፍ ነዉ ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ትልቅ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ግብርና ሴቶችና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በፍትሐዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሴቶችን ማብቃትና የሚታዩ ክፍተቶችን መሙላት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በካሳሁን አሰፋ
