ቆይታከእኛጋር!

Spread the love

የዚህ ወር “ቆይታ ከእኛ ጋር” እንግዳችን ፕሮግራም

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊና የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ቤተልሔም ተሾመ ጋር ስለመሬት ይዞታ ምዝገባ(ካዳስተር) ምንነትና አስፈላጊነት፣ በዘርፉ ከክልሉ ምስረታ ወዲህ የተከናወነው ተግባራት፣የመሬት ይዞታን በካደስተር የመመዝገብ ጠቀሜታው ፣ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫና መፍትሔዎች በሚመለከት ከክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል። እንደሚከተለው ቀርቧል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን (መ/ኮ)፡ የቆይታ ከእኛ ጋር ፕሮግራም እንግዳ ለመሆን ፍቃደኛ ስለሆኑ ከልብ እናመሰግናለን።

ወ/ሮ ቤተልሔም ፦እናንተም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።

መንግስት ኮሙኒኬሽን፦የመሬት ይዞታ ምዝገባ(ካዳስተር) ምንነትና አስፈላጊነት ቢያስረዱኝ

ወ/ሮ ቤተልሔም፦በከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ(ካዳስተር) ማለት፥ በአዋጅ ቁጥር 818/2006 አንቀፅ 2 ንኡስ አንቀፅ 18 መሰረት “የመሬት ይዞታ መብት፣ ክልከላና ሃላፊነት በህጋዊ ካዳስተር መዝገብ፣ የሚመዘገቡበት ሂደት ” ነው፡፡

የህዝብና የመንግስት ንብረት የሆነውን የከተማ መሬት ሃብት በዘመናዊ አሰራርና ቴክኖሎጅ በመታገዝ ለላቀ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውልና፤ ከተሞች የመሬት አስ/ር ስርዓት ያልያዘ በመሆኑ ህገወጥነት በመቀነስ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ባረጋገጠ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ ክልሉ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ መጠነ ሰፊ የቅድመ ዝግጅትና የትግበራ ሥራ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን፦የከተማ መሬት ይዞታ ለምን ይመዘገባል?

ወ/ሮ ቤተልሔም፦ የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባ መነሻ ሁኔታዎች መሬት ልዩ አያያዝና አስተዳደር የሚሻ ንብረት በመሆኑ፣ መሬት በማምረት የሚገኝ አለመሆኑ፣ መጠኑ የማይጨምር በመሆኑ፣ ራሱንም ሊተካ የማይችል ንብረት መሆኑ፤ ከቦታ ቦታ የማይንቀሳቀስ መሆኑ፣ የመሬት ልማትና አስተዳደር ለመልካም አስተዳደር ችግር እና ለኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ ሆኖ በመቀጠሉ፤

የመሬት ይዞታ መረጃ ለተለያዩ ጉዳዮች ግብዓት በመሆኑ፤ (ለህጋዊ፣ ለአስተዳደራዊና ለኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎችን እንዲሁም ለከተማ ፕላንና ለመሬት ልማትና አስተዳደር) የከተሞችን ገቢ በእጅጉ የሚያሳድግ በመሆኑ መመዝገብና ማዘመን ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፦ይህንኑ አስመልክተው ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ ምን እየተሰራ ነው?

ወ/ሮ ቤተልሔም ፦ባለፉት ሦስት ዓመታት ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ በከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ (ካዳስተር) ዘርፍ ስራውን ለመጀመር ብዙ የቅደሜ ዝግጅት ስራዎች ተከናውኗል ።

ከክልሉ ምስረታ ወዲህ በአምስት የክልሉ ከተሞች ማለትም ሚዛን ዓማን፣ ቴፒ፣ ማሻ፣ ቦንጋ፣ ታርጫ የተጀመረው የመሬት ይዞታ መረጃ የማጥራት ተግባር በ2016 3 ከተሞችን በመጨመር እንዲሁም በያዝነው የ2017 በጀት ዓመት 2 ከተሞችን በመጨመር በአጠቃላይ በ10 ከተሞች እየተሰራ ይገኛል።

ስራው በተጀመረባቸው ከተሞች ተግባራትን ለማቀላጠፍና ስለ ይዞታ ምዝገባ ጥቅም ለህብረተሰቡ አስቀድሞ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተፈጠረው መድረክና በተሰራው የግንዛቤ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ማሳተፍ ተችሏል።

በተደረገው የዝግጅት ምዕራፍና መረጃ የማጥራት ሂደት ላይ ከ65,000 በላይ ነባርና ሰነድ ያላቸው ይዞታዎች በከተሞች መኖሩን በማረጋገጥ ፣የመሬት ልከት መነሻ ነጥቦችን በመለየት ሁለተኛ ደረጃ የመሬት መቆጣጠሪያ ነጥቦችን መትከል፣ከሀገራዊ መረጃዎች ጋር በሳትላይት በማናበብ የማስተሳሰር ስራ ተሰርቷል ።

በዚህም መሠረት ከ22,000 በላይ ይዞታዎችን በአስር ከተሞች እስከ ቦታው ወርዶ ማካለል፣መለካትና የማረጋገጥ ስራ በማከናወን፤ ከተረጋገጡት ይዞታዎች መካከል ለምዝገባ ብቁ የሆኑ 11,000 ቁራሽ መሬቶች ምዝገባ ተካሂዶ በህጋዊ ካዳስተር ማዕቀፍ ማስገባት የተቻለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 1ሺህ ቁራሻ መሬት በቦንጋ ከተማ በካዳስተር ሲስተም ተመዝግቦ ለህብረተሰቡ አግልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ህጋዊ ሆነው ከተመዘገቡት ይዞታዎች በሰርተፍኬት፣በአገልግሎት ክፍያ፣በስም ዝውውር፤ለብድርና ዋስትና አገልግሎቶችን በመስጠት ተግባሩን በጀመሩ ከተሞች ከ40 ሚለየን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን፦የመሬትን ይዞታን በካደስተር የመመዝገብ ጠቀሜታው ምንድነው?

ወ/ሮ ቤተልሔም፦ ከተማ መሬት ምዝገባና መረጃ ሥርዓት ማስፈን ፋይዳ ብዙ ቢሆንም ዋና ዋናዎቹ ለይዞታ ባለቤትነት ዋስትና ያረጋገጣል፤ የተረጋጋና አስተማማኝ የሆነ የይዞታ ሥርዓት በማስፈን ክርክሮችን በእጅጉ ይቀንሳል፣ የመሬትና መሬት ነክ የንብረት ታክስ ሥርዓት ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን ለማገዝ፣ ግብይትና ባለቤትነት ዝውውርን ለመቆጣጠር፣በግብይቱ መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ተገቢ ገቢ እንዲያገኝና ህብረተሰቡም የልማት ተጠቃሚ እንድሆን ለማድረግ እንዲሁም ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመቆጣጠር ይረዳል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን፦ ይህ ስራ በክልል ምንም ከሌለበት እንደ መጀመሩ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ይኖሩ ይሁን?

ወ/ሮ ቤተልሔም፦ በክልሉም ሆነ በየከተሞቹ የሀብት እጥረት ፣ በዘርፉ የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል እጥረት ፣የቅየሳ መሣሪያ ያለመኖር እንዲሁም የባለድርሻ አካላት የተግባሩን ጠቀሜታ በውል ተረድተው ትኩረት ያለመስጠት ስራውን በተፈለገው ልክ ለማስኬድ ማነቆ ሆኖ ተገኝቷል ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን፦ቀጣይ መደረግ አለበት የሚሉት መልዕክት ቢያስተላልፉ?

ወ/ሮ ቤተልሔም፦ ቀጣይም በየደረጃው የሚገኙ ከተሞችና የባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባን ማዘመን ዘርፌ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በውል በመገንዘብ ለሥራው የሚሆን ሀብትን መመደብ፣ የሰው ኃይልን ማሰልጠንና መመደብ፣ለስራ የቅየሳ መሣሪያ መግዛት፣ የሲስተም ሰርበር መግዛት እንዲሁም ለህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤን በማስጨበጥ በክልሉ ሁሉም ከተሞች በትኩረትና በቅንጅት መስራት ይገባል።

የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደርን ለማሻሻል የዘርፉ አመራር በከተማው ውስጥ ያለውን የመሬት መጠንና አይነት ለይቶና አውቆ ለሌሎች የልማት ሥራዎች ለማዋል የሚያግዝ በመሆኑ በቁርጠኝነት መምራት ያስፈልጋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *