




የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች የህዝቦችን ወንድማማችነት በሚያጠናክርና ዘላቂ ሰላምን ሊያሰፍን በሚችል መልኩ እልባት ለመስጠት እንደሚሰራ ተገለጸ፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 4ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ አንደኛ መደበኛ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡
በስብሰባው፤ የማንነት አስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው 2017 በጀት ዓመት እቅድ፤ የወልቃይት፣ ራያና ጠለምት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከአካባቢው መስተዳድርና ነዋሪዎች ጋር ውይይት በማካሄድ በአካባቢው ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ መተማመን የመፍጠር፤ ተፈላጊ መረጃዎችን የማጥራት ስራ በማከናወን ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ በምክር ቤቱ በኩል ትዕዛዝ እንዲሰጥ ሪፖርት የማቅረብ፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሳኔውን አፈጻጸም በየጊዜው ለምክር ቤቱ እያቀረብ እንዲያስገመግም የማድረግ ሥራዎች በበጀት ዓመቱ እንደሚከናወኑ ተገልጿል፡፡
በአፋርና ሱማሌ ክልል ሶስት ቀበሌዎች (ገዳማይቱ፣ እንዱፎ እና አዳይቱ) የሚነሳው የወሰን ይገባኛል ጥያቄዎችን በመመርመር ለውሳኔ የሚረዱ መረጃዎችን በማደራጀት ዘላቂ እልባት ለመስጠት እንደሚሰራም ተመላክቷል።
ከዚህም ባሻገር ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርበው ውሳኔ ያገኙ ነገር ግን በውሳኔው መሰረት እስካሁን ያልተተገበሩ ጥያቄዎች እልባት ያገኛሉ ተብሏል፡፡ ይህ ሁሉ ሲተገበር የህዝቦችን ወንድማማችነት በሚያጠናክርና ዘላቂ ሰላምን ሊያሰፍን በሚችል መልኩ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬ ስበሰባው የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ፤ የመንግስታት ግንኙነት የዴሞክራሲ አንድነትና የህገ መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ፣ የማንነት አስተዳደር ወሰን እና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ፣ የህገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል፣ የህገ መንግስት ትርጉምና ውሳኔ አፈጻጸም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት በማድረግ አጽደቋል፡፡ በተጨማሪም ከሕገ መንግስት አጣሪ ጉባዔ የህገ መንግስት ትርጉም በሚያስፈልጋቸውና በማያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ የውሳኔ ሀሳብ ምርምሮ አጽድቋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል፡፡
