




የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ አመት ምስረታ በዓል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ክልላዊ ማጠቃለያ ”የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና”በሚል መሪ ሀሳብ በቦንጋ ከተማ በፓናል ውይይትና ሌሎች መርሃ-ግብሮች ተከብሯል።
በውይይቱ ”የብልጽግና ፓርቲ የአምስት አመታት ጉዞ”ላይ ያተኮረ ሰነድ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ በአቶ በላይ ተሰማ ቀርቧል።
ሰነዱ ሀገሪቱ ከለውጡ በፊትና በኃላ ያለው መሠረታዊ ጉዳዮች፤ ብልጽግና ፓርቲ ከተመሠረተ ወዲህ በኢኮኖሚ፤ በፖለቲካና በማህበራዊ ጉዳዮች ስራዎች፤የተመዘገቡ ስኬቶች፤ በሂደቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫን ዳሳሳ ያደረገ ነው።
የፓናል ውይይት ተሳታፊዎች ፓርቲው በሁሉም ዘርፍ የህዝቡ የልማት ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በውይይት ችግሮችን ለመፍታት በሽግግር ፍትህና በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የጀመረው ተግባር የሚመሰገንና መጠናከር የሚገባ እንደሆነም ተናግረዋል።
ፓርቲው በውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች ሳይበገር በመደመር ጉዞ በክልሉ ከትናንት ያደሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እየመለሰ የሚገኘው ስራዎችን ማጠናከር ይገባልም ብለዋል።
አሁንም በስራ ዕድል ፈጠራ፣ ኑሮ ውድነት፣ የረጅም ጊዜ ተጀምሮ የቆዩ መንገድ ልማት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት፣ በጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲሁም ሠላምና ጸጥታ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ አመልክተዋል።
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በላይ ተሰማ በበኩላቸው ፓርቲው እንደሀገር ባጋጠመው ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎች ሳይበገር ሀገርን ከመበታተን ያዳነ ፓርቲ ነው ብለዋል።
በፓርቲው መሪነት ክልሉ በትላልቅ መድረኮች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲያረጋግጥ ዕድል ተፈጥሯል ያሉት አቶ በላይ ተሰማ ፓርቲው ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲሁም የኮንትሮባንድ ንግድና ዝውውር ለመከላከል ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።
ፓርቲው የተጀመረው ጉዞ እንዲጠናክር የአመራር፣ የአባላት እንዲሁም የደጋፊዎች አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም የገለጹት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው።
በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት፣ በቡና ምርታማነትና ጥራት ማሳደግ፣ በሰው ተኮር በጎ አገልግሎት ስራዎችና በህብረ-ብሔራዊ እና በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ሰፊ ስራዎችን ማከናወኑንም አቶ ማስረሻ አብራርተዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንደገለጹት ፓርቲው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ስብራቶችን ማረምና ማከም የሚያስችሉ ሰፊ ስራዎችን አከናውኗል።
በፓርቲው መሪነት በክልላዊና ሀገራዊ ፕሮጀክት፣ በሰላምና ፀጥታ፣ በስንዴ ልማትና በሌሎች ልማት ስራዎች የተጀመረው ስራ ቀላል የሚባል አይደለም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በክልሉ ያለ እምቅ አቅም በመጠቀም እና ሰፊ አምራች ህዝብ ተሳትፎን በማሳደግ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በኑሮ ውድነት ቅነሳ፣ በአንዳንድ አከባቢ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን መፍታት፣ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም በዜጎች ስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
በፍቅር ከበደ
