




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስትና የፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ አካሂዷል።
በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋትና በጉድለት የተነሱ ችግሮች ፈጥኖ በማረም የህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ነው በመድረኩ ማጠቃለያ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የገለጹት።
የከተማና የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ መጀመርና ማጠናቀቅ የቀጣይ ጊዜ የትኩረት አቅጣጫ መኾኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የገጠር ሽግግርንም ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በየደረጃው የድጋፍ አግባብ በማጠናከር የንቅናቄ ተግባራትን በተሻለ መልኩ መፈጸም እንደሚገባ ያስገነዘቡት ዶ/ር ነጋሽ፥ የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ፈንድ በሁሉም መዋቅር ተከፍተው ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመቋቋም ተግባር መጠናከር አለበት ብለዋል።
የብሄራዊ መታወቂያ (ፋይዳ) ምዝገባን በክልሉ በልዩ ንቅናቄ በመፈጸም ዕቅዱን ለማሳካት የተለያዩ ማኅበራዊ መሠረቶችን በመጠቀም እንደሚገባ ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያሳሰቡት።
የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተደራሽነት ለማስፋት በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶ/ር ነጋሽ በተለይ የአዲስ አባል ማፍራት ተግባር ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው ብለዋል።
በክልሉ የተጀመረው የገቢ አሰባሰብ ስርዓት መጠናከር እንዳለበት ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በተለይም በከተሞች በልዩ ትኩረት መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በክልሉ ለተገኘው የአፈጻጸም መሻሻል፣ በዝግጅት ምዕራፍ በአመራር መካከል የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለመፈጠር በተከታታይ የሰጡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የጎላ ድርሻ እንደነበረ ያነሱት የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን ናቸዉ።
በየደረጃው የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመለየት አመራሩ በቁርጠኝነት መፍታት እንደሚገባ በማስገንዘብ የፓርቲውን ተልዕኮዎችን ለማሳካት ተጨማሪ ትጋት፣ ፈጠራና ፈጥነት እንዲሁም ዝላይ መታከል አለበት ብለዋል አቶ ፍቅሬ።
የብልጽግና ፓርቲ በ2018 ዓ/ም ከተስፋ ወደ ሚጨበጥ ብርሃን ለመሻገር ያስቀመጠውን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት በየደረጃው ያለው አመራር ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ በየቦታው የሚገኙ የአርሶአደር ማሰልጠኛ ተቋማት ወደ ተግባር በማስገባት የክህሎት ስልጠና መስጠት እንደሚገባም አቶ ፍቅሬ ያስገነዘቡት።
በቀጣይ በክልሉ በተለዩ የአስፈጻሚ ተቋማት የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ያለበት ደረጃ በጥልቀት በመገምገም የአግልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል እንደሚሰራም አቶ ፍቅሬ ተናግረዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
