




የቤንች ሸኮ ዞን ምክር ቤት 4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።
የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ጌድዮን ኮስታብ ጉባኤውን ሲከፍቱ ባስተላለፉት መልዕክት ምክር ቤቱ በሕገ-መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሕግ ማውጣት፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎችን በማከናወን የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የሕግ አውጪው፣ የአስፈጻሚውና የሕግ ተርጓሚው አካላት የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ይገመገማል።
በየደረጃው ከሕዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት የሚገመገሙ ሲሆን፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶች በቀጣይ በልዩ ትኩረት እንደሚታዩ ተመላክቷል።
የወረዳ ምክር ቤቶችን የማስፈጸም አቅም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና ወጥ የሆነ አሠራር ለመዘርጋት በቀጣይ በትኩረት እንደሚሠራ ተገልጿል።
አፈ ጉባኤው አክለውም ይህ ጉባኤ በዞኑ ውስጥ ታላላቅ የልማት ስኬቶች በተመዘገቡበት ወቅት መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ከነዚህም መካከል በ”ገበታ ለአገር” ፕሮጀክት የተገነባው የደንቢ ኢኮ ሎጅ እና የጉራፈርዳ ወረዳ የገጠር ኮሪደር መንደር ተመርቀው አገልግሎት መጀመራቸው፤የአማን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ተጠናቆ ለምረቃ መቃረቡ፤
ብልጽግና ፓርቲ 7ኛውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ በሆነ መልኩ ለማካሄድ ዝግጅቱን በጨረሰበት ወቅት መሆኑ ናቸው።
በመጨረሻም፣ የምክር ቤት አባላቱ በውይይቱ ላይ በንቃት በመሳተፍ የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጡ ጥሪ ቀርቧል።
አፈ ጉባኤው መላው የዞኑ ነዋሪዎች በመራጮች ምዝገባ ወቅት ተመዝግበው በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ቀርቦ ይፀቃል፣ የዞኑ ምክር ቤት የ2018 ዓ.ም የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ እንደሚገመገም እንዲሁም ልዩ ልዩ ሹመቶች እንደሚጸድቁ ይጠበቃል ሲል የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
