ሪፖርታዥ
በተያዘው የምርት ዘመን ከ71 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ባለስጣን አስታወቀ



በ2017 የበጀት ዓመት የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አዲስ ማሳን ማስፋትና በነባር ማሳ የተለያዩ ምርታማነት ማሻሻያ ፓኬጆች መተግበርና ምርጥ የቡና ዘር የማዘጋጀትና ማቅረብ ሥራዎች በሰፊው ማከናወን መቻሉንና ከክልላችን ፍላጎት ባሻገር ለተለያዩ ክልሎች የቡና ምርጥ ዘር ማቅረብ የተቻለ መሆኑንና በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ በቂ ዝግጅት መደረጉ ተመላክቷል።
የቡና ተከላ አፈጻጸምና ምርት አሰባሰብ ስራዎች ላይ ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጠን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ: በ2017 በጀት ዓመት በስግሰጋ፤በሞተ ከዳና አዲስ ተከላ በአጠቃላይ 88.5 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅደው 87.9 ሚልዮን (የዕቅዱን 99%) ማከናወን ተችሏል ብለዋል።
ተከላው በሁለት ዙር የሚከናወን መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ከ2017 ዓ.ም የተሻገረ በሐምሌ እና 30.4 ሚልዮን የቡና ችግኝ በሐምሌና ነሐሴ ወራት ከክረምቱ አረንጓዴ አሻራ ልማት ጋር አቀናጅተው ለመትከል ታቅደው ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 23 ሚሊዮን የቡና ችግኝ (75%) መተከሉን ገልጸዋል።
በክልላችን በአራቱም የቡና አመራረት ዘይቤዎች ማለትም የጫካ፣ የከፊል ጫካ፣ የጓሮና ዘመናዊ ተከላ በአጠቃላይ ከ597ሺ ሄ/ር በላይ የቡና ማሳ ሽፋን እንዳለ የጠቆሙት አቶ አስራት በ2017 በጀት ዓመት 17 ሺህ 918 ሄክታር በአዲስ ተከላ መሸፈኑን ገልፀው የማሳ ማስፋት ስራ በያዝነው የበጀት ዓመት እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።በ2017 የበጀት ዓመት ከክልላችን 48 ሺህ 153 ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ በያዝነው ዓመት ከ71ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን ገልፀዋል።



ቡና እንደ ሀገር የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ግንባር ቀደም የግርና ምርት መሆኑን ገልጾ በባለፈው የበጀት ዓመት እንደ ሀገር 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ያወሱት አቶ አስራት ከዚህም የክልላችን ምርት ከፍተኛ ድርሻ ከያዙት ውስጥ የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመዋል።
የ2018 በጀት ዓመት ሥራ ሲጀመር የቡና ምርት ዝጅት፤ጥራት አጠባበቅና የግብይት ሥርዓቱ ከአውሮፓ ህብረት ከደን ጭፍጨፋ ነፃ ምርት ግብይትን ለመተግበር ያወጣዉ ደንብ ጋር ተጣጥሞ እንድተገበር ለማስቻል ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር እና ከክልሉ ቡና አዘጋጆች ማህበር ጋር በመቀናጀት ለአምራቾች፤ አቅራቢዎችና ባለድርሻ አካላት ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በማካሄድ እንቅስቃሴ ንቅናቄዉ በየደረጃዉ እስከ ታች እንድወርድ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነዉ ብለዋል ዋና ደይሬክተሩ።
ከአምራች አርሶ አደሮች ባሻገር የኢንዱስትሪዎች ቅድመ ዝግጅት እየተገመገመ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የማጠቢያ ማሽኖቻቸው፣ አልጋና አውድማ እንዲሁም የመጋዘን ዝግጅታቸው ከወዲሁ ተፈትሾ የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት እንዲታደስላቸው እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የክህሎት ክፍተት ላለባቸው የተግባር ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት እንደተደረገ ገልጸዋል።
የተሳለጠ የግብይት ሰንሰለት ለመዘርጋት እና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ ለቡና ግብይት ብቻ የተከለለ የመጀመሪያ ደረጃ ግብይት ማዕከላት ሊጠናከር ይገባል ያሉት አቶ አስራት በዚህም ህጋዊ የሆኑ አካላት የዕለቱን ዋጋ ለጥፈው እንዲገበያዩ ይደረጋል ብለዋል።
እስካሁን ባለዉ ሁኔታ በዋናነት የቡና ምርት በቀጥታ ትስስር የግብይት አሠራር መሠረት አቅራቢ ነጋዴዎች ከላኪዎች ጋር ቀጥታ ትስስር በመፍጠር ምርቱ ቀጥታ ከወረዳ ተሸኝቶ በቴፒ፣ በሚዛን አማን እና በቦንጋ ከተሞች በሚገኙ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ሽኝት ማዕከላት በኩል ተመዝግበው ወደ ቦንጋ የምርት ጥራት ምርመራና ሠርቴፊኬሽን ማዕከል እንደሚላኩ ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም በሀገር ደረጃ ሁለት የጥራት ምርመራና ሠርተፊኬሽን ማዕከላት እንደነበሩ ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ ያልተማከለ አሰራርን ለመዘርጋት በተደረገው ሪፎርም እንደ ሀገር በርካታ የክልል ከተሞች እንድስፋፋ እየተደረገ ያለ ሲሆን በክልላችንም ከቦንጋ ከተማ በተጨማሪ በሚዛን-አማን እና ቴፒ ከተሞች አገልግሎቱ የሚጀምር መሆኑን ጠቁመው ይህም የተገልጋዩን እርካታ ክፍ ያደርጋል ብለዋል።
የክልላችን የቡና ምርት ጥራት ከደረጃ 3 በታች እንዳይወጣ ልዩ ትኩረት ተሠጥቶ ይሰራል ያሉት አቶ አስራት ከዘርፉ የሚጠበቀውን የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የክልላችን ብሎም የሀገራችንን ብልፅግና እውን ለማድረግ እንድቻል አምራች አርሶ አደሮች፣ የንግዱ ተዋኒያን፣ አልሚ ባለሀብቶች እንዲሁም በየእርከኑ ያሉ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እንድሁም የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት በምርት ዝግጅት፤ጥራት አጠባበቅ እና ህገ ወጥ የቡና ዝውውርን በመከላከል ረገድ ተገቢ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
