ቆይታ ከእኛ ጋር!

Spread the love


በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክርቤት የግጭት አፈታት ስትራቴጂ ዙሪያ የተደረገ፡፡


የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ስርዓት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና እኩልነት መከበር ትኩረት የሰጠ ነው፡፡ በ1987 ዓ.ም የወጣው የኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ-መንግሥት በርካታ የቡድን እና የግለሰቦች መብቶች እውቅና እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ በዚህ ህገ-መንግሥት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በጋራ አብሮ ለመኖርና ለማድግ ያስችላቸው ዘንድ የግለሰብና የብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች መሠረታዊ መብቶች መከበር የግድ አስፈላጊ እንደሆነ በመግቢያው ላይ ከማስቀመጡም በላይ በአንቀጽ 8(1) ላይ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች መሆናቸውን ደንግጓል፡፡ በመሆኑም በህገ-መንግስቱ መሠረት የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ተቋቁሞ የህገ-መንግስቱን የበላይነት የማስከበር፣ የብሔረሰቦች እኩልነትን የማረጋገጥ እና የፌዴራሊዝም ስርዓቱን የመጠበቅ፣ ሕገ-መንግስቱን የመተርጎም፣ የብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብትና ጥያቄዎችን የመፍታት፣ እንዲሁም በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የመፍታት ስልጣንና ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በክልል ደረጃም በተለይ ብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ባሉባቸው ክልሎች የብሔረሰቦች ምክር ቤት ተቋቁሞ ከኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በተናበበ መልኩ በክልሉ የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና እኩልነት ጉዳዮችን በበላይነት ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልም 13 ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያሉበት ክልል በመሆኑ የብሔረሰቦች ምክርቤት ተቋቁሞ በክልሉ ህገ-መንግስት የተሰጠውን ስልጣንና ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የግጭት አፈታትና ሠላም ግንባታ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ወደ ስራ ለማስገባት አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቁን ገልጿል።
ስትራቴጂው ግጭቶችን በጊዜያዊ መፍትሄ ከመቆጣጠር በላይ ወደ አዎንታዊ ማህበራዊ ለውጥ ለመቀየር የሚያስችል አዲስ አቀራረብ እንዳለውም ተገልጿ፡፡
ለመሆኑ ይህ የግጭት አፈታት እስትራቴጂ ምን አዲስ አቅጣጫ ይዞ መጣ? በሚለው ዙሪያ ከክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ከፍተኛ ኤክስፐርት ጋር ቆይታ አድርገናል።
መልካም ንባብ
መ/ኮ ለግዜዎት አመሰግናለው፤ ራሶን ያስተዋውቁ፡፡
 እንግዳችን፡- አበበ ገብሬ እባላለው፤ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት የብሔረሰቦች ትስስር፣ ግጭት አፈታትና ሠላም ግንባታ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ነኝ፡፡
መ/ኮ በመጀመሪያ ይህን የግጭት አፈታት ስትራቴጂ ማዘጋጀት ለምን አስፈለገ?
 አቶ አበበ፡- በክልሉ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች የሕዝቦችን አንድነት፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ላይ እንቅፋት እየሆኑ መጥተዋል። በተለይ በአርብቶ አደር አካባቢዎች ተከታታይ ግጭቶች መታየታቸው ለሰው ሕይወትና ንብረት ጉዳት አስከትሏል። ስለዚህ ግጭቶችን በጊዜያዊ መፍትሄ ብቻ ሳይሆን ከስር ከመንስኤያቸው ጀምሮ በዘላቂነት ለመፍታት የተደራጀ አቅጣጫ ለመፍጠር ስትራቴጂው ተዘጋጅቷል።
መ/ኮ፤- ከዚህ ቀደምት በነበረ የግጭት አፈታት ሥራ ላይ የታዩ ክፍተቶች ምን ነበሩ?
 አቶ አበበ ፡- ቀድሞ የነበረው ሀገራዊም ሆነ ክልላዊ እስትራቴጂ የሚያተኩረው ግጭትን ከተከሰተ በኋላ በመፍታት ላይ እንጂ የሠላም ግንባታንና የሁሉን ክልሎች አካባቢ ነባራዊ ሁኔታ ያካተተ አልነበረም በአብዛኛው ጊዜ ግጭትን ከተፈጠረ በኋላ መፍታት ላይ ያተኮረ ነበር። ይህ ደግሞ ለከፍተኛ ሀብት ብክነት እናጊዜን የሚበላ ነው ።የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት የነበረው ቢሆንም ቀልጣፋና ከሁሉም አካባቢመረጃ ሰጪ አልነበረም፣ ባለድርሻዎችንም በአግባቡ አልካተተም። አሁን የተዘጋጀው እስትራቴጂ ከቀድሞ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል የነበረውን በመውሰድና አሁን የተደራጀንበትን ክልል ነባራዊ ሁኔታ እንድሁም ሀገራዊ የግጭት መከላከልና ሠላም ግንባታ እስትራቴጂ እንደመነሻ ወስዷል።
መ/ኮ በክልሉ ውስጥ ዋና ዋና የግጭት መንስኤዎች ምን እንደሆኑ ትገልጹልን?
 አቶ አበበ ፡- በክልሉ ውስጥ ዋና ዋና የግጭት መንስኤዎች ድህነት፣ የሀብት ሽምያ፣ የወሰን አለመግባባት፣ የመልካም አስተዳደር እጥረት እና የሰላም ባህል አለመዳበር ከፍተኛ ሚና አላቸው። እነዚህን መንስኤዎች በተገቢ መንገድ ካልተካከልን ግጭት ሊቀጥልና ሊስፋፋ የምችል ጉዳይ ነው።
መ/ኮ አዲሱ ስትራቴጂ የሚለየው በምንድነው?ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማስፈን ምን አዲስ አቅጣጫ ይዞ መጣ?
 አቶ አበበ ፡- በአዲሱ ሰትራቴጂ ግጭትን ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ወደ አዎንታዊ ማህበራዊ ለውጥ ለመቀየር የ“ግጭት ትራንስፎርሜሽን” አቀራረብን እንከተላለን። የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት፣ የክትትልና ግምገማ መንገድ፣ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ተሳትፎን ዋና መርሆ አድርጎ ይሰራል በተለይምየእስትራቴጂዉ ማዕከላዊ ነጥብ ግጭቶችን በመቀነስ አሊያም ጉዳት በማያደርሱበት ደረጃ በማድረስ ለዘላቂ ልማትና ሠላም መሠረት መጣል ነዉ ሥለዝህ ሰዶ ከማሳደድ ይልቅ ሳይቃጠል በቅጠል የሚል ብሒላችንን ያሰቀድማል ማለት ችላለው።
መ/ኮ፤- ወጣቶችና ሴቶች በዚህ ሂደት ምን ሚና ይኖራቸዋል?
 አቶ አበበ ፤- ወጣቶችና ሴቶች በግጭት እና በሰላም ሂደቶች ውስጥ በአብዛኛው ተጎጂ ወይም ተመልካች ብቻ ይሆናሉ። አዲሱ አቀራረብ እነሱን እንደ ተሳታፊ እና አስተዋፅኦ ሰጪ መመልከቱ አዎንታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ይታመናል። ወጣቶችና ሴቶች የሰላም ግንባታ ዋና ኃይል ናቸውና በማህበራዊ ውይይቶች፣ በሰላም ኮሚቴዎች እና በአጠቃላይ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ፕሮጀክት ውስጥ ከፍ ያለ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ትኩረት ተሰጥቷል።
መ/ኮ ለስትራቴጂው ተግባራዊነት ምን ክልላዊ አስቻይ ሁኔታ ኣለ ?
 አቶ አበበ ፡- ከአስቻይ ሁነታ አንፃር አሁን የባለድርሻ አካላት ሚና እየጎላ መምጣቱ ክልላችን ድልብ ማህበራዊ ሀብት ያለው መሆኑና ሀገር በቀል ዕውቀት እንደዋንኛ የግጭት መፍቻ ሆኖ እየተሠራበት መሆኑና በእስትራቴጂው ትኩረት የተሠጠው መሆኑ ከቅንጅትም አንፃር ባህላዊ ፍርድቤቶች ቁርሾን በሚያስቀርና የህዝቦችን ትስስር የሚያጠናክር እስትራቴጂ የሚከተል መሆኑና የክልሉ መንግስት ክልላዊ እስትራቴጂዉን ወደመሬት ለማውረድ ቁርጠኛ መሆኑ እንድሁም የክልሉ ህዝብ ማህበራዊ ውቅር ከግጭት ይልቅ ለሠላምና አብሮነት ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑ እንደአስቻይ ሁኔታ ተወስዷል፡፡
መ/ኮ ከስትራቴጂው ምን ውጤት እንጠብቅ?
 አቶ አበበ ፡- አዲሱ የግጭት አፈታት ስትራቴጂ ግጭቶች በቅድመ ማስጠንቀቂያ መለየትና ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ፤ የሕዝቦች አንድነትና ትስስር እንዲጠናከር የሰላም ባህል እንዲዳብር፤ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንዲፋጠን የሚያስችል ውጤት ያሰገኛል ብለን እናምናለን፡፡
መ/ኮ. የመጨረሻ መልዕክቶ ምንድነው?
 አቶ አበበ:- አመሰግናለው ቀደም ብሎ ስለ ግጭት ግንዛቤ መፍጠር ለችግሮች ፈጣን ምላሽ እና ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅ ያግዛል። ይህ ደግሞ የሕዝቦች አንድነት ይጠናከራል፣ በሰላም ልማትም ይፋጠናል ስለዚህ ሰላምን መጠበቅም ይሁን ማስጠበቅ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ኃላፊነት ስለሆነ በመግባባትና በመከባበር ችግሮቻችንን እንፍታ፤ ዘላቂ ሰላም እንገንባ እላለው፡፡ አመሰግናለው።
መ/ኮ እኛም እናመሰግናለን፡፡

በበረከት ኢዮብ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *