




የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አከባቢ ቢሮ ከአርብቶ አደር አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ለንግድና ገበያ ልማት ባለድርሻ አካላት በሚዛን አማን ከተማ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።
በስልጠናዉ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አርብቶ አደርና ቆላማ አከባቢ ቢሮ ኃላፊ አቶ መቱ አኩ ቢሮው በአርብቶ አደር አካባቢዎች የተለያዩ አጋር አካላትን በማስተባበር መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁሟል።
የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በውስን ዘርፎች ከመሰማራት ይልቅ በብዝሃ ዘርፎች እንዲሰማሩ የተለያዩ የኢኮኖሚ ምንጮችን ማለማመድ ያስፈልጋል ብለዋል።
በደላሎች ጣልቃ ገብነት ምክንያት አርብቶ አደሩ ከምርቱ መጠቀም የሚገባውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እያገኘ አለመሆኑን ያብራሩት ኃላፊው ለዚህም በአርብቶ አደር አካባቢ የግብይት ማዕከላትን ማስፋፋትና የግብይት ሰንሰለቱን ማሳለጥ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ ገልፀዋል።
የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የገበያ ልማት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ አሰገደች ወልደየስ በበኩላቸው የገበያ መሰረተ ልማት ጉድለትን ለማስተካከል ቢሮው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አከባቢ (LLRP2) ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ደረጀ በቀለ ፕሮጀክቱ ላለፉት 5 ዓመታት በክልሉ በተመረጡ 5 ወረዳዎች በአርብቶ አደር አካባቢዎች በመሰረተ ልማት ሟሟላትና በአመለካከት ቀረፃ በርካታ ልምዶችን መስራቱን ገልፀው በተገኘው ልምድ መሰረት የማህበረሰቡ ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
በስልጠናው ከክልሉ ከካፋ ዞን፣ ከቤንች ሸኮ ዞንና ከምዕራብ ኦሞ ዞን የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በንጉሴ ወልደየስ
