በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የካሳቫ ምርትን እሴት በመጨመር ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነዉ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የካሳቫ ምርትን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከመዋል ባለፈ፣ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተቀናጀ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ ተጠቆመ።

በኦሞ አዲስ አግሮ ፕላትፎርም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ በኢትዮጵያ ካሳቫ ኮንትራት አምራቾችና ኤክስፖርተሮች ማህበር እንዲሁም በኮመታ እርሻ ልማት ባለሀብቶች ማህበር ትብብር የተዘጋጀው ይህ ስልጠና፤ በካሳቫ አመራረት፣ በዘመናዊ እርሻና በአግሮ-ፕሮሰሲንግ ዙሪያ ትኩረቱን አድርጎ በሚዛን አማን ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን እንደገለጹት፤ መንግስት የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን በመፍታት በግብርናውና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል። በተለይም ቀደም ሲል ከውጭ ይገባ የነበረውን ስንዴ በሀገር ውስጥ በስፋት አምርቶ ወደ ውጭ መላክ መጀመሩን እንደ አብነት የጠቀሱት ዋና ተጠሪው፣ በካሳቫ ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶችም ምርቱን በጥራትና በስፋት በማምረት ለኤክስፖርት ዝግጁ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

አቶ ፍቅሬ አክለውም ክልሉ ያለው አስተማማኝ ሰላም እና በቅርቡ ወደ ስራ የሚገባው የሚዛን አማን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ክልሉን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጉት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ካሳቫ ኮንትራት አምራቾችና ኤክስፖርተሮች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ምስጋናው አስማማው በበኩላቸው፤ የካሳቫ ተክል ያለውን ዘርፈ-ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያህል እስካሁን በትኩረት እንዳልተሰራበት ጠቁመዋል። “ዘርፉን ለማሳደግ በማህበር ተደራጅቶና ተባብሮ መስራት አማራጭ የሌለው መንገድ ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኮመታ የካሳቫ እርሻ ልማት ባለሀብቶች ማህበር ያከናወናቸውን ተግባራት ያደነቁት ዶ/ር ኤርሲዶ ለንደቦ፤ ማህበሩ ስልጠናውን በማመቻቸት ባለሀብቶችን ለጋራ ስኬት ማነቃቃቱ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ በሚገኘው በዚህ ስልጠና ላይ የማህበሩ አባል ባለሀብቶች፣ የባንክ ስራ አስኪያጆች፣ የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል። ስልጠናው በክልሉ ያለውን የካሳቫ ምርት አቅም ወደ ላቀ የገበያ ደረጃ ያሸጋግራል ተብሎ ይጠበቃል ሲል የቤንች ሸኮ ዞን ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *