cs v

Spread the love

የቤንች ሽኮ ዞን ፀጥታ ምክር ቤት የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ላይ ውይይት አካሄዷል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን እንደገለፁት የዞኑን ሰላም አስተማማኝ በሆነ መንገድ ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራዊ አቅጣጫዎችንና የጋራ የአፈፃፀም ስልቶችን ለማስቀመጥ የዛሬው ጉባኤ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል።

በብዙ ጥረት የተገነባውን ሰላም በየወቅቱ ካልተገመገመ የገነባነውን ሰላም በትንሽ ስህተት ልናጣው እንችላለን በማለት ወቅቱን ጠብቆ የፀጥታ ጉባኤ ማድረግ የሁሉም ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ አጽኖት ሰተዋል።

የጸጥታ ስራው ውጤታማ እንዲሆን የፖሊስና የጸጥታ አካላት ብቻ ሳይሆኑ የባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሁሉም ማህበረሰብ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ወንጀልን የመከላከል ስራን ማጠናከር ፣ የህገወጥ ኮንትሮባንድ ንግድ ፣ የጦር መሳሪያና ሌሎችም ቁሳቁሶች ዝውውርን መግታት፣ የቀይ እሸት ቡና ሽምጠጣ ስርቆትን መከላከል፣ ከአጎራባች ክልል ድንበር ተሻጋሪ ዝርፊያና የጸጥታ ችግር ጉዳይ ብሎም የጥፋት መንስኤዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል ብለዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ በሰላም ወቅት መስራት አለብን ብለዋል።

በየመዋቅሮች የሚፈፀመዉን ወንጀል ለመከላከል ዝግጁዎች መሆን እንደሚገባ አውስተው ድንበር አልፎ የሚመጣን አካል ተይዞ በህግ አግባብ ሊጠየቁ እንደሚገባ አጽኖት ሰጥተዋል።

የዞኑ ሰላምና ፀጥታ ሚሊሻ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች በዛብህ ዞናዊ የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ ለጉባኤው ሪፖርት አቅርበዋል።

በቀረበው የዞኑ የፀጥታው ምክር ቤት ሪፖርት የህግ የበላይነትን ከማስከበር ፣ ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ፣የቀይ እሸት ቡና ሽምጠጣና ስርቆት ፣ ሐይማኖት ተቋማት ጋር የሚስተዋሉ ችግሮች፣ አጎራባች ክልል ጋር ድንበር ተሻጋሪ ዝርፊያዎች ጉዳይ እንዲሁም ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ክትትል በመቆጣጠር የተሰሩ ሥራዎች ቀርበዋል።

የጸጥታ ምክር ቤት እንደ አስፈላጊነቱ የወረዳዉ ወይም ከተማዉን ሀዝብ ደህንነት ጉዳይ በየ15 ቀኑ ምልከታ የሚደረግበት እና መዘናጋት የማይገባ ተግባር መሆኑን አቶ ዘማች ገልፀዋል።

አክለውም የማህበረሰቡን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚያስችል የተቀናጀ የፀጥታ ዕቅድ በማውጣት፣ የፀጥታ አካላትና የማህበረሰቡን ትስስር ማጠናከር ትኩረት የሚሰጠው ተግባር እንደሆነ ጠቁመዋል።

ጉባኤው በቀረበው የፀጥታ ሪፖርት ላይ ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ የአከባቢውን ሠላምና ፀጥታ ይበልጥ ለማጽናት የሚያስችሉ ሀሳብ እና አስተያየት ሰጥተዋል።

በመድረኩ በርካታ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን በቀጣይ የህዝቡን ሠላም ለማጽናት እና ዘላቂ ዕድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚሰሩ ስራዎች ተለይተው በፀጥታው ምክር ቤት ጉባኤ የጋራ መግባባት መደረሱን የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *