“የላቀ የመከላከል አቅም ያለው የሰው ኃይል መገንባት ተችሏል” — ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

Spread the love

የኢፌዴሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ፣ በጄትና በሄሊኮፕተር የበረራ ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ አብራሪዎችንና የቴክኒክ ባለሙያዎችን በድምቀት አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፣ ተቋሙ ተለዋዋጭ የሆነውን የዘመኑን የጦርነት አውድ በሚገባ የተረዳና የላቀ የመከላከል ብቃት ያለው የሰው ኃይል መገንባት መቻሉን ገልጸዋል።

በዕለቱ በጄት እና በሄሊኮፕተር በቂ የበረራ ሰዓት ያጠናቀቁ ተማሪዎች የተመረቁ ሲሆን፤ ለእጩ መኮንን ሰልጣኞችም የዲፕሎማ፣ የበረራ ክንፍ እና የምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ ተሰጥቷል።

በአየር ኃይል ቴክኒክ ኮሌጅ በአቪዬሽን ዘርፍ በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠኑ ባለሙያዎች በዲፕሎማ ተመርቀዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ሁለት ሴት አብራሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከጎረቤት ታንዛኒያ የመጡ ሰልጣኞች መካተታቸው የተቋሙን ቀጠናዊ ተመራጭነት የሚያሳይ ሆኗል።

አየር ኃይሉ የሰው ኃይል ልማትን፣ የመሠረተ ልማት ግንባታንና የትጥቅ ዘመናዊነትን ጎን ለጎን እያስኬደ እንደሚገኝ ዋና አዛዡ አረጋግጠዋል።

ተመራቂዎቹ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበርና ለኢትዮጵያ ሰማይ አስተማማኝ ጥበቃ ለማድረግ ለተጀመረው የሰው ኃይል የማፍራት ተልዕኮ “አዲስ ጉልበት” እንደሚሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጿል።

ይህ የ90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አየር ኃይሉ ካለፈው ታሪኩ እየተማረ ለወደፊቱ ይበልጥ እየዘመነ መምጣቱን ያበሰረ ክስተት ሆኖ አልፏል ሲል የዘገበው ኢቢሲ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *