



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በመጀመሪያ አጀንዳነት የተመለከተዉ የቀረቡለትን የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን ነዉ።
በዚህም ካላቸዉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ፣ ከሚያስገኙት ስራ ዕድል አኳያ ከ1 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 36 የግብርና እና 3 የኢንዱስትሪ በአጠቃላይ 39 የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ላይ ከተወያየ በኃላ ወደ ሥራ እንዲገቡ ወስኗል።
ምክር ቤቱ በሁለተኛ አጀንዳነት የተመለከተዉ የቀረቡለትን ረቂቅ ደንቦች ነዉ።
በዚህም የማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣ ረቂቅ ደንብ ላይ በገጠርና በከተማ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአካባቢያቸው የሚገኙ የማዕድንና የኢነርጂ ሀብቶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብ፣ በማልማትና በመጠቀም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በመልካም አስተዳደር ለውጦች ሊይ የበኩላቸውን እንዲወጡ በማስቻል ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ አስፈሊጊ መሆኑን በመረዳት በቀረበዉ ረቂቅ ደንቡ ላይ ተወያይቷል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠልም የተመለከተው የክልሉን ፖሊስ አባላት መተዳደሪያ ደንብ ሲሆን በዚህም ክልሉ የተያያዘዉን የሠላም፣ የልማት እና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማፋጠን በሚደረገዉ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ዉስጥ የበኩለን ድርሻ ሊያበረክት የሚችሉ የፖሊስ ተቋም እና የፖሊስ አባል መገንባት በማስፈለጉ ደንቡ መዉጣቱን ተመልክቷል።
በክልሉ የጥብቅና አገልግሎት ለሚሰጡ የህግ ባለሙያዎች ከቢሮው አገልግሎት ለማግኘት የሚጠበቁባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሁም የሚያገኟቸው አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን የአገልግሎት ክፍያዎች በግልፅ መዘርዘር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መስተዳድር ምክርቤቱ የቀረበለትን የጠበቆች ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር ደንብም ላይም ተነጋግሯል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ የደን ልማት ጥበቃና አጠባበቅ ረቂቅ ደንብ ላይ የመከረ ሲሆን በክልሉ የሚገኘውን የደን ሀብት በመንከባከብ፣ በመጠበቅ፣ በማልማትና ቀጣይነት ያለው የአጠቃቀም ስሌት በመቀየስ ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን እና በደን ምርት ውጤቶች አቅርቦት እና ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትኩረት ሰጥተው ለመስራት ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ረቂቅ ደንብ መሆኑን መክሯል ።
መስተዳድር ምክርቤቱ በመጨረሻ የተመለከተው የከተሞች የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ በወጣ ደንብ ሲሆን የደረቅ ቆሻሻን አካባቢያዊ ተቀባይነት ባለው ሳይንሳዊ ዘዴ መያዝና መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ከተሞቻችን ጽዱ፣ ውብና ለነዋሪዎቻቸው ምቹ የስራ ቦታና የመኖሪያ አካባቢ እንዲሆኑ ለማድረግ በማሰብ የቀረበዉ ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቷል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ የቀረቡለትን ረቂቅ ደንቦች ላይ በዝርዝር ከመከረ በኃላ የተሰጡት ሀሳቦች ተካተዉ ስራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል ፡፡
