ክልሉ አስፈጻሚ ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እየተገመገመ ነዉ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት በበጀት ዓመቱ በ1ኛ ሩብ ዓመት በክልሉ በአስፈጻሚ ተቋማት የተከናወኑ ተግባራትን የክልሉ መንግስት በቦንጋ ከተማ መገምገም ጀምሯል።

በአፈጻጸም ግምገማው የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበጀት ዓመቱ ለማከናወን የተለጠጠ ዕቅድ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል ።

የተለጠጠውን ዕቅድ ለማሳካትም ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ በመከተል ተግባራትን ማሳካት እንደሚገባ ተናግረዋል ።

በአንደኛው ሩብ ዓመት በተቋማት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮችን ትኩረት በማድረግ ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል ።

በዚህም የተገኙ ውጤቶችን በመገምገምና በ2ኛው ሩብ ዓመት ትኩረት የሚሹትን ተግባራት በመለየት በትኩረት መስራት ይገባልም ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አሁን ላይ በክልሉ የዝናብ ሁኔታ ያልተቋረጠ በመሆኑ በመስኖ ልማት ስራዎች ያለውን አመቺነት በመጠቀምና የደረሱ ሰብሎችን እንዳያበላሽ ከወዲሁ በየደረጃው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል ።

በክልሉ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በሩብ ዓመቱ የተገኘውን ውጤታማነት ለማስቀጠል አመራሩና ባለሙያዎች ትኩረት በመስጠት ተግባሩን ሊደግፉ ይገባል ብለዋል።

በትምህርትና በጤና ልማት ስራዎች በንቅናቄ የተጀመሩ ስራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊመሩ እንደሚገባም አሳስበዋል ።

በተለይም የትምህርት ጥራትን የማስጠበቅና የወባ በሽታን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።

ከዝናብ መቀጠል ጋር በተያያዘም በየአካባቢው የመንገድ መሠረተ ልማቶች ብልሽት እየገጠማቸው በመሆኑ በክልሉ ያሉ የገጠር መንገድ ድስትሪክ ጽ/ቤቶች ከወዲሁ የጥገና ስራዎችን ማከናወን ይገባቸዋል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ።

በክልሉ በሰላምና ጸጥታ ስራዎች የተጀመሩ አበራታች ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል ።

የክልሉ መንግስት የአስፈጻሚ ተቋማት የአንደኛው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት እየተገመገመ ነው ።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *