
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 21 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ አለመረጋጋቶች በባህር ትራንስፖርት አገልግሎት እንቅስቃሴ የፈጠሩትን ጫና በመቋቋም ውጤታማ ስራ ማከናወኑንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር ደምሰው በንቲ ለኢዜአ እንደገለፁት፥ በበጀት ዓመቱ አገልግሎትን ለማስፋትና ተደራሽነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
ድርጅቱ በመርከብ፣ በጭነት አስተላላፊነት፣ በወደብና ተርሚናል እንዲሁም በኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፎች በርካታ ስራዎች ሰርቷል ብለዋል።
በመጀመሪያው በጀት ዓመትም ከአገልግሎቶቹ 20 ነጥብ 46 ቢሊየን ብር ለማግኘት አቅዶ 21 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል።
አፈጻጸሙ የእቅዱን 103 በመቶ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ 62 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡
በጭነት ማጓጓዝ አገልግሎት ብቻ 860 ሺህ 387 ቶን ገቢና ወጪ እቃዎችን ማጓጓዝ እንደተቻለ ጠቅሰዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚከናወነው የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ በመርከብ የሚካሄድ እንደመሆኑ በዓለም የተከሰቱ አለመረጋጋቶች ቀላል የማይባል ተፅዕኖ መፍጠራቸውን አብራርተዋል።
ይህን ዓለም አቀፋዊ ችግር በመቋቋም ረገድ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ በሩብ ዓመቱ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ነው የገለጹት።
የድርጅቱን አሰራር ለማዘመንና አገልግሎቱን ቀልጣፋ ለማድረግ በቴክኖሎጂ የታገዙ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በቀጣይም ድርጅቱ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሳደግ ተጨማሪ 6 ግዙፍ መርከቦች እና 205 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ማቀዱን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል
