የኢትዮጵያ ሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፦አቶ አበበ ማሞ

Spread the love

‘የህልም ጉልበት፤ለእመርታዊ እድገት ” በሚል መሪ ቃል በቴፒ ማዕከል ላለፉት አስር ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው 3ኛ ዙር የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ በስኬት ተጠናቋል።

በማጠቃለያ መርሃግብር ላይ ተገኝተው ለአመራሩ የስራ መመሪያ የሰጡት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ የኢትዮጵያ ሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥና የህብረተሰቡን ህይወት ለማሻሻል የአመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ህልማችንን ለማሳካት በተገቢው መተለምና የወል ትርክትን መያዝ እንዲሁም መተግበር ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው በማለት የወል ትርክት፣የመደመር መንገድና የመሃል ፖለቲካን በሚመለከት በማጠቃለያው ላይ በስፋት አንስተው አመራሩ የይቻላል መንፈስን ተላብሶ መምራትና ማስተባበር እንዳለበት አሳስበዋል አቶ አበበ።

ሁሉም ተግባር ውጤታማ ልሆን የሚችለው አመራሩ በአስተሳሰብና በተግባር አንድ መሆን ሲችል ነው ብለዋል።

ከስልጠናው ማግስት ጀምሮ በንድፈ ሃሳብና በመስክ ጉብኝት ያገኙትን ግንዛቤ ወደ መሬት በማውረድ የህብረተሰቡን ህይወት ለማሻሻል በትጋት መስራት ያስፈልጋል ሲሉም በአፅንኦት አንስተዋል አቶ አበበ።

ዘላቂነት ያለው ልማት የሚመጣው በህዝቦች አንድነትና በጠለቀ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ትስስር መሆኑን የገለጹት አቶ አበበ ዘላቂና አዎንታዊ ሠላም ለልማታችን እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን እንዲሁም ለህግ የበላይነት መስፈን ትልቅ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።

ጠንካራና ዘላቂነቱ የሚያስተማምን የሀሳብና የተግባር አንድነትን መገንባት ቁልፍ የፓርቲያችን ተልዕኮና ተግባር አድርጎ በመውሰድ እና ግንዛቤን በማዳበር ለላቀ ውጤት መረባረብ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።

አመራሩ የተገኙ ስኬቶችን በአግባቡ በመገንዘብና ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ ተጨማሪ ስኬቶችን ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅበታል ሲሉ አንስተዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ሸካ ዞን ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አለማየሁ አለሙ በበኩላቸው አመራሩ በትርክት እመርታ ፤ በፖለቲካ ፤ በምጣኔ ሀብት ፤ በውጪ ግንኙነት ፤ በፀጥታና ደህንነት ፤ በሥነ-ምግባራዊና ሰብዓዊ እመርታ ለማምጣት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ በውጤታማነት በመምራትና አስተባብሮ በማስፈጸም ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ብልጽግና ምዕራፍ ለማሻገር የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

ስልጠናው ዓለም አቀፋዊ ፣ አህጉራዊ፣ ቀጠናዊና ሀገራዊ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታዎችን ተገንዝቦ ወቅቱን የዋጀና ውጤታማ አመራር ለመፍጠርና የጋራ መግባባት

የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የምንሰራቸው ስራዎች በሙሉ የህዝቡን ቅቡልነትና እርካታን የሚያረጋግጡ መሆን መቻል አለባቸው ሲሉም ገልፀዋል አቶ አለማየሁ።

አቶ አለማየሁ አያይዘውም አርቀን በማለምና አልቀን በመስራት ለሀገራችን ሁለንተናዊ ብልፅግና መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በዞኑ በርካታ ሀብት የሚገኝ በመሆኑ እነዚህን አቀናጅቶ በመምራትና በመጠቀም በበጋ ስንዴ፣በሌማት ትሩፋት በፍራፍሬ፣በቅመማ ቅመም፣በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ተግቶ በመስራት ሀብት በመፍጠር ኢኮኖሚያችንን ማሳደግ መቻል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የሸካ ዞን ሁሉም ወረዳና ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ አመራሮች እንዲሁም በቴፒ ከተማ ከሚገኙ የፈዴራል ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ200 በላይ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በስልጠናው የተሳተፉ ሲሆን የጋራ ተግባቦት በመፍጠር ተጠናቋል ሲል የዘገበው የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *