



የክልሉ ፍትህ ቢሮ፣ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እና ኦዲት ቢሮ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ውይይት በቦንጋ ከተማ እያደረጉ ነው።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቤተልሔም ዳንኤል የሙስና ወንጀል የህዝብንና የመንግስትን ኃላፊነት ባልተገባ መልኩ በመጠቀም የሚፈጸም በመሆኑ ውስብስብና ለምርመራ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቀ የመጣ በመሆኑ የመከላከሉና ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረጉ ስራን ተቋማት በልዩ ትኩረት፣ እውቀትና ትብብር መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የሙስና ወንጀል የመቆጣጠር ስኬት ወንጀለኞችን ተጠያቂ ከማድረግ ባለፈ አለአግባብ የተመዘበረ ሀብትን ማስመለስን ይጨምራል ብለዋል።
ይህን ተግባር ይበልጥ ፈታኝና ውስብስብ እንዲሆን የሚያደርገው አንዳንድ የሙስና ወንጀለኞች ሀብቶችን ከሀገር ውጭ የሚያሸሹበት ሁኔታ ሊፈጠር በመቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የሙስና ወንጀል የመከላከሉና ተፈፅሞ ሲገኝ ወንጀለኞችን በህግ ተጠያቂ የማድረጉና ሀብት የማስመለሱ ስራ በትኩረት ካልተሰራ በመንግስት እና በህዝብ ላይ የሚያሳድረው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጫና ክፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሙስናን የመከላከሉ እና ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረጉ ስራ በተፈለገው ልክ ግቡን እንዲመታ ተቋማት ስራቸውን በተናጠል አማከናወን ይልቅ በትብብርና በቅንጅት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ይህን የቅንጅት ስራ መስረት እንዲይዝና ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግ ተቋማቂ ቅርፅ እንዲይዝ ማድረግ ወይም አደረጃጀት መፍጠር ያስፍልጋል፡፡
የዚህ መድረክ ዋነኛ ዓላማ የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ የፖሊስ ተቋማት፣ የፍትህ ተቋማት እና የኦዲት መስሪያ ቤት ሙስናን የመከላከል፣ ምርመራ የማካሄድ፣ ክስ የመመስረት እና የተመዘበረ ሀብት የማስመለሱን ስራ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የስነ-ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ጥምርት ማቋቋምን መሰረት ያደረገ ነው፡፡
ጥምረቱ ተቋማት ተቀራርበው የሚሰሩበትን ስርዓት የሚዘረጋና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ሙስናን በሚመለከት ቀልጣፋና ውጤታማ የሆነ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡
ተቋማቱ ስልጠና መስጠትን፣ መረጃ መቀባበልን እና የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል ማድረግን የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችል ጥምረት መሆኑን ወይዘሮ ቤተልሔም ዳንኤል ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳግም ዳንኤል እንደገለጹት ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በግምገማ ተለይተዋል።
በተቋማት መካከል የቅንጅት ማነስ ችግር እንዳለ ገልጸው ፤ መድረኩ ጥምረትን በማጠናከር የበለጠ ውጤታማ ለመሆን የሚያስችል ነው ብለዋል።
በክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ አራቱ ተቋማት በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሰነድ አቅርበው ውይይት እየተደረገ ነው ሲል ቦንጋ ኤፍኤም ዘግቧል።
