ባለፉት ሶስት ወራት ከ200 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ማስገባት መቻሉን የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ አስታወቀ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬከተር ዶ/ር ጌታቸው ወልያብ የክልሉ መንግሥት ለማዕድን ልማት ዘርፍ ለሰጠው ልዩ ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱንና አፈጻጸሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የተሻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት ከ350 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ነው ዶ/ር ጌታቸው የጠቆሙት፡፡

በዚህም በሩብ ዓመቱ የአምራችነት ፍቃድ ካላቸው እና ከልዩ አነስተኛ ማህበራት 87.5 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ታቅዶ ባለፉት ሶስት ወራት ከ200.54 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል።

በክልሉ 199 ልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራች፣ 7 ባህላዊ ወርቅ አምራች እና 32 ወርቅ አቅራቢዎች መኖራቸውን የጠቀሱት የኤጄንሲ ዋና ዳይሬከተር ዘርፉ ከሚያስገኘው ከሮያልትና ከተለያዩ የገቢ አማራጮች 44 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ነው የተናገሩት፡፡

በዘርፉ የሚስተዋለውን መሠረታዊ ችግሮች በዘላቂነት በመፍታት በቀጣይም የተሻለ የወርቅ ምርት ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ እንዲቻል ኤጄንሲው የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ስራዎችን የመስራት፣ የጸጥታና አካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በሚያደርግበት መልኩ እንደሚሰራም አመላክተዋል፡፡

እያንዳንዱ የወርቅ አቅራቢና አምራች ማህበራት በተቀመጠው የህግ ማዕቀፍና የአሠራር እና ውል እንዲሁም በተቀመጠው ዕቅድ መሠረት ማከናወን እንዳለበትና በዚህም መሠረት ስራውን የማያከናውን ወርቅ አምራች አቅራቢ ማህበራት በአሠራር ስርዓት እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንሲ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የአምራቾችን ለመደገፍና ግንዛቤ ለማሳደግ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *