የገጠር መሬት አያያዝና አጠቃቀም በዕቅድ የተመራ እንዲሆን ማስቻል እንደሚገባ ተገለጸ።

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ደን፣ አከባቢ ጥበቃ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ FOLUR ፕሮጅክት በእናት ዛፍ ልየታ፣ የዛፍ ዘር አሰባሰብና ዝግጅት ዙሪያ ለባለሙያዎችና ለማህበራት የተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በቦንጋ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።

የFOLUR ፕሮጀክት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሀዝቦች ክልል፣ በካፋ እና ቤንች ሸኮ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 6 ወረዳዎች፣ 30 ቀበሌያችን ተጠቃሚ ያደረገ እንደሆነ ነው፤ በቢሮው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ በእውቀቱ ሃይሌ (ዶ/ር) የገለጹት።

በእንግሊዝኛ፥ Preventing Forest Loss, Promoting and Integrating Sustainability into Ethiopia’s Coffee Value Chains and Food Systems ፕሮጀክት በክልሉ ከደን ውድመት ነፃ የሆነ የቡና ልማት ሥራን ከዘላቂ የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ስርዓት ጋር በማስተሳሰር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ዶክተር በእውቀቱ ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ በታቀፉ ቀበሌዎች የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ስርዓትን ከደን ውድመት ነጸ ከሆነው የቡና ልማት ፕሮግራም ጋር ማስተሳሰር አንዲሁም የተራቆቱ ቦታዎችን መልሶ የማልማት ልምምዶችን በማበረታታት ረገድ ፕሮጀክቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስተባባሪው ተናግረዋል።

የቡና ልማትና ደን ሀብት ከክልሉ ህዝብ የአኗኗር ዘይቤ ጋር በሰፊው የተቆራኙ እንደሆነ ያስረዱት ዶክተር በእውቀቱ፥ተፈጥሮን የማይጎዳ የተመጋገበ የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ስርዓት ስትራቴጂ መሠረት ያደረገው ፕሮጀክቱ፥ በ2017 በጀት ዓመት 500 ሄክታር የቡና ማሳ ጉንደላ ማከናወኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ የደን ዘር ባንክ ያለመኖሩ በደን ዘር ዝግጅት ላይ ክፍተት መፈጠሩን የጠቆሙት ዶክተር በእውቀቱ፥ ፕሮጀክቱ ይህንን መሠረታዊ ክፍተት ለመሙላት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በፕሮጀክቱ ቀበሌያቸው አሳታፊ የደን አስተዳደር ማህበራት ተቋቋመው አየሰሩ መኾኑን የጠቆሙት ዶክተር በእውቀቱ፥ በዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ ከ7ሺህ በላይ ሀይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ለአባላቱ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በስልጠናው ከፕሮጀክቱ ወረዳዎች የተወጣጡ አርሶአደሮች፣ የአሳታፊ ደን ባለሙያዎች እና ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *