በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር እና የጤና ተቋማት የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመቀነስ በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ።

Spread the love

በክልሉ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭትን ለመቀነስ በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ የክልሉ ጤና ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያደረገው ምክክር ተጠናቋል።

በምክክሩ መድረክ በክልሉ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች የአፈጻጸም ሪፖርታቸውን አቅርበው አስገምግመዋል።

በቀረበው የአፈጻጸም ሪፖርት ስርጭቱን ለመቀነስ ጥረቶች መኖራቸውና አሁንም ቅንጅታዊ አሰራሮች ይበልጥ የሚዳብሩበት እንደሆነም በመድረኩ ተነስቷል።

ሪፖርት ከቀረቡባቸው ከተማዎች በተለይም በሚዛን አማን ፣በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ፣በምዕራብ ኦሞ ዞን ቤሮ ወረዳና ቦንጋ ከተማ የስርጭቱ መጠን ጎልቶ የታዩባቸው መሆኑ ተገምግሟል።

ስርጭቱን ለመቀነስ በግሎባል ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የምርመራ ስራዎችን በማጠናከር ቫይረሱ በደማቸው የተገኙ ዜጎች የመድኃኒት ህክምና እንዲጀምሩ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑም ተነስቷል።

በክልሉ ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ፕሮግራም አማካሪ የሆኑት አቶ አበበ ደምሴ በክልሉ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት መጠን ከዞን ዞን የሚለያይ ሲሆን የስርጭት መጠኑን ለመቀነስ በቅንጅት ተረባርቦ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

በክልሉ ከ14 ሺህ በላይ ዜጎች ቫይረሱ ይኖርባቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁት ውስጥ በምርመራ ከ8 ሺህ በላይ ዜጎች ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው እንደተገኘባቸውም አቶ አበበ ተናግረዋል ።

በተያዘው 2016 የበጀት ዓመት 9 ወራት ውስጥ 789 ቫይረሱ በደማቸው እንደተገኘና ከዚህም ውስጥ 65 ከመቶ የሚሆነው ከ15_24 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ መሆናቸውንም አቶ አበበ ገልጸዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊና ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሌ ዘውዴ መድረኩን ሲያጠቃልሉ በጤና ተቋማት የሚስተዋለውን ግዴለሽነት በማስወገድ የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።

የበሽታው ስርጭት በክልሉ ትላልቅ ከተሞች መጠኑ እየሰፋ በመሆኑ በሀይማኖት ተቋማት ፣በትምህርት ቤቶች፣ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ ሊሰራበትም ይገባል ብለዋል።

በክልሉ እየመጡ ካሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ተከትሎ ከሚኖረው የሰው ሀይል ፍሰት አንጻር ከወዲሁ ትኩረት በመስጠት የምርመራ ስራዎችን በማከናወን ቫይረሱ የሚገኙባቸውን ፈጥኖ ህክምና እንዲጀም መድረግ ትኩረት ሊሰጠውም ይገባል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ህክምና አግኝተው መኖር የሚችሉ 64 ዜጎች በ10 ወራት ውስጥ መድሀኒታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ባለመደረጉ መሞታቸውን አብራርተዋል ።

የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመቀነስ በሚደረገው ሁሉ አቀፍ ርብርብ ባለድርሻ አካላት ከመቼውም ጊዜ በላቀ በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው አቶ ሀይሌ አሳስበዋል ።

በኤች አይ ቪ ተጋላጭነታቸው በሚበዛባቸው አካባቢዎች የተዘጋጀው የአፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ የተለያዩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ በመስጠት መድረኩ ተጠናቅቋል ።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *