





በምርጫው ሂደት በነፃነትና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ድምፃችንን መስጠት ችለናል ሲሉ የመስቃንና ማረቆ ሁለት ምርጫ ድምፃቸውን የሰጡ መራጮች ተናገሩ።
የድጋሚና ቀሪ ምርጫ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ቁሳቁሶች ተሟልተው በተለያዩ አካባቢዎች በዛሬው እለት መራጮች ድምጽ ሰጥተዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም የመስቃንና ማረቆ ሁለት የምርጫ ክልል ነዋሪዎች ከማለዳው ጀምረው የድጋሚ ምርጫ አካሂደዋል።
የምርጫ ሂደቱን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው መራጮች ሂደቱ ፍፁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ገልጸዋል።
ከመራጮቹ መካከል አቶ ኢብራሂም ኡመር፣ አቶ ሸምሱ ሲራጅ እና ሰኢድ አሻሞ፤ በምርጫው ሂደት በነፃነትና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ድምፃችንን መስጠት ችለናል ሲሉ ተናግረዋል።
ሌሎች ድምፃቸውን ሲሰጡ ያገኘናቸው ሙሉነህ ኒኔ፣ ሸምሱ መሀመድ፣ ይፍቱስራ ቃበቶ እና ባንችይርጋ ጀማል የምርጫ ሂደቱ የተረጋጋ፣ ሰላማዊና ጥሩ መስተንግዶ የታየበት ነው ብለዋል።
በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ወቅት የጸጥታ እና የተዓማኒነት ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች ድጋሚና ቀሪ ምርጫ ለማካሄድ ቀደም ብሎ በምርጫ ቦርድ ዝግጅት መደረጉ ይታወሳል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
