




3ኛው የሸኮ ብሔር የዘመን መለወጫና የምስጋና በዓል ቲካሻ ቤንጊ የፓናል ውይይት መድረክ በሸኮና አካባቢው ምሁራን የጥናትና ምርምር ማህበር አዘጋጅነት በሸኮ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የሸኮና አካባቢው ምሁራን የጥናትና ምርምር ማህበር የበላይ ጠባቂ አቶ ወንድሙ ኩርታ በፓናል ውይይት መድረኩ እንደተናገሩት ባህል የአንድ ማህበረሰብ የማንነት መገለጫ ፣ ደስታውን ፣ ሀዘኑን ፣ ምስጋናውን እንዲሁም አብሮነትና አንድነቱን የሚገልጽበት ስርዓት ነው ብለዋል።
ቲካሻ ቤንጊ ምንም እንኳ ለበርካታ አመታት በአደባባይ ባይከበርም የብሔሩ ተወላጆች በግለሰብ ደረጃ ሲያከብሩት የቆየ ባህል መሆኑን ገልጸዋል።
ቲካሻ ቤንጊ የሸኮ ብሔር ሀገር በቀል እሴት እንጂ የማንንም ፈለግ የተከተለ አይደለም ያሉት አቶ ወንድሙ ምሁራን ማህበሩም ባህሎች እንዲጎለብቱና ሀብት እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የምሁራን ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ወንዱ ታደሰ በበኩላቸው የሸኮ ህዝብ ከተፈጥሮ ሀብት ጋር ተስማምቶ ከመኖር ባሻገር ደን ለሸኮ ብሔር ምግቡ ፣ ልብሱ ፣ መኖሪያው ፣ ማረፊያውና ኢኮኖሚው መሆኑን ገልጸዋል።
የሸኮ ብሔር ሰላም ወዳድና የራሱ የሆነ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት ያለው መሆኑን ገልጸው ምሁራን ማህበሩም ህዝቡን በማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ተጠቃሚ እንዲሆን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የፓናል ውይይቱ ቀጥሎ እየተካሄደ ሲሆን በዶክተር አራጌ ይመር እና በዶክተር ፍሬህይወት ባዩ የሸኮ ብሔር ባህላዊ እሴቶች ላይ የፓናል ውይይት መነሻ ሰነድ እየቀረቡ ይገኛሉ ሲል ቤንች ሸኮ ቴቪ ዘግቧል።
