





የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ በቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያና 5 ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡
የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ምትኩ አስፋው እንዳገለጹት÷የዲጂታል ዓለም ላይ አብሮ ለመጓዝና ተወዳዳሪ ለመሆን ማሰልጠንና ማብቃት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የሀገራችን ኢትዮጵያ የ2030 ዲጂታል ዕቅድ እውን ለማድረግ በ5 ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ የሚሰጠው ተከታታይነት ያለው ስልጠና ዜጎች የዲጂታል እውቀት አገኝተው ተጨማሪ ሥራ እንዲፈጥሩና የኢኮኖሚ አቅማቸው እንዲያድግ የሚያስችልላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ የመንግሥት አገለግሎት ዲጂታላይዝድእየሆነ መምጣቱን የጠቆሙት አቶ ምትኩ ዜጎችን በዚህ ውስጥ ማሳተፍና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት 6 ወራት ከ246 ሺህ 436 ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት መሆናቸውንና በቀጣይ 6 ወራት 1ሚሊየን 700 ሺህ ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 110 ሺህ በላይ 5 ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ሰልጣኞችን በመመዝገብ ስልጠና ለመስጠት ግብ ተጥሎ እስከ አሁን 28ሺህ 900 ሰልጣኞች ተመዝግበው እንደ ክልል 7ሺህ 953 ሰልጣኞችን ሰርትፋይ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
አሁንም የተያዘውን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በዳታ ሳይንስ እና በፕሮግራምንግ እንዲሁም በሌሎችም አጫጭር ስልጠናዎች የማስጣቱ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የካፋ ዞን ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታደሰ የዲጂታል ዓለምን ለማስተዋወቅ መንግሥት ካመጠባቸው ሀገራዊ ኢንሼቲቮች በፋይዳ መታወቂያና 5 ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ተጠቃሾች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ለ17 ሺህ 200 ለሚሆኑ 5 ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ለመስጠት ታቅዶ ባለፉት 6 ወራት ለ5ሺህ 200 ሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ሰርትፋይ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ከፋይዳ ድጂታል መታወቂያ አኳያም በበጀት ዓመቱ ለ711ሺህ 917 ዜጎች የድጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ታቅዶ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን አፈጻጸሙ 140 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች የድጂታል መታወቂያ ባለቤት ሆነዋል ይህም ከታቀደው ዕቅድ አንፃር ዝቅተኛ በመሆኑ በቀጣይ ወራት ዕቅዱን ለማሳካት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡
የቦንጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአይሲቲ መምህርና የ5ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ አስተባባሪ አቶ ዋለልኝ ክብረት፤ የ5 ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ኢትዮጵያ በ2030 ለመድረስ ያቀደችውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስርዓት ለማስቀጠል የኮሌጁ ዋና ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኮሌጁ የ5 ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ከተጀመረ ሁለት አመታትን ማስቆጠሩን ገልጾ በዚህም ለአጠቃላይ ለግቢው ማህበረሰብና ከግቢ ውጭ ያለውን በማሳተፍ በሰፊው ስልጠና መሰጠቱን 150 በላይ ሰልጣኞችን በአራቱ ሰርቲፊኬት ሰርትፋይ ማድረግ የተቻለ መሆኑን አንስቷል፡፡
አለማችን ወደ ዲጅታል ቴክኖሎጂ እየሄደች በመሆኑ የግቢያችን ሠረተኞችና አጠቃላይ ማህበረሰብ የዲጅታል ቴክኖሎጂ እንዲያውቅ ኢትዮ-ኮደርስ እንደ አንድ መነሻ እንደሆነና ተጨማሪ ስራዎችን እንዲሰሩ የሚያችላቸውን መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
