
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልካም ምኞት መግለጫቸው እንደገለጹት ኢትዮጵያ ብዝሀ ማንነትና ባህሎች ተከባብሮና ተቻችሎ የሚኖሩባት የብዝሃነት ማዕከል መሆኗን በመጥቀስ ከነዚህ ውብ ባህልና ዕሴቶች አንዱ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
ኢሬቻ የክረምት ወራት አልፈው መጸው ሲገባ ፈጣሪ የሚመሰገንበት በታላቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበር በዓል በመሆኑ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብን እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ የኢሬቻ ባህላዊና ታሪካዊ ዕሴት በማጉላት ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢሬቻ ሁሉም በአንድነት የሚያከብረው የምስጋና በዓል በመሆኑ ሁላችንም የበዓሉ እሴቶች በሚያዘው አኳኋን ማክበር አለብን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የኢሬቻ በዓል የቱሪዝም ዘርፉን በማጠናከር ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ያለው ፋይዳም ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን በዓል በሀገር አቀፍና አለምአቀፍ መድረኮች ማስተዋወቅ፣ መጠበቅና መንከባከብ እንዲሚገባ ጠቁመዋል።
ኢሬቻ አንድነትና ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት/እኅትማማችነት በማጠናከር ለሠላም ዕሴት ግንባታ የጎላ ፋይዳ እንዳለው ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉ በህዝቦች መካከል ያለውን ግኑኝነት በማጠናከር መተሳሰብ የሚገነባ እንደሆነም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በስተመጨረሻም በዓሉ የፍቅር፣የአንድነት፣የመተሳሰብና የአብሮነት በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸዉን ገልጸዋል።
