ክልሉ ከሚያመነጨው ሀብት አንፃር አጠቃላይ የገቢ መሠረቶችን በመለየት ገቢ መሰብሰብ ያስፈልጋል፦ ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት አመት ያለፉት ሁለት ወራት የደረጀ ሐ እና ለ አፈፃፀም እንዲሁም የቀሪ ወራት የገቢ አሰባሰብ ላይ ከክልል እና ከዞን አስተባባሪ አካላት እንዲሁም ከገቢ ሴክተር ኃላፊዎች ጋር የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ አካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ክልሉ ከሚያመነጨው ሀብት አንፃር አጠቃላይ የገቢ መሠረቶችን በመለየት ገቢ መሰብሰብ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካትና ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ ከማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አንፃር ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሯል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም ሀብት የመፍጠር እና ገቢ የመሰብሰብ ዕድሉ በጣም ሰፊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ውስጥ ታክስ በአግባቡ በመምራትና በማስተዳደር ገቢ መሰብሰብ እንደሚገባ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ የፖለቲካ አመራሩም ልዩ ትኩረት ለዘርፉ እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡

በትምህርት እና በጤና ተቋማት አካባቢ እንደ ክልል ቀላል የማይባል ገቢ የሚሰበሰብበት መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ የሚሰበሰበው ገቢ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ተገቢ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት በ2017 በጀት ዓመት የህብረተሰቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እንዲቻል የክልሉን ወጪ 60 በመቶ በገቢ በመሸፈን ኢኮኖሚ ከሚመነጨው ሀብት 10.1 ብሊየን ብር ገቢ ለመሠብሰብ ከክልል ጀምሮ እስከ ወረደ እና ከተማ አስተዳደር ድረስ በቁርጠኝነት ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ የክልሉን ገቢ በተለይም የጥረት ተደራሽ ገቢን ከፍ ለማድረግ ከዚህ በፊት የፀደቁ ደንቦችና መመሪያዎችን በአግባቡ በመተግበር በዘንድሮው ከሚሰበሰበው አጠቃላይ ገቢ ቀጥታ ያልሆነ ታክስ 45 በመቶ እንዲሸፍን ግብ የታጠለ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

የገቢ አሰባሰብን ውጤታማ ለማድረግ ሁለቱ ደረጃዎች ሀ እና ለ ግብር ከፋዮች ቁጥር መጨመር አስፈላጊ በመሆኑ የግብር ከፋዮች ደረጃ ሽግግር በማድረግ የታክስ ህጉን ለግብር ከፋዮች በተገቢው በማስተማርና ለታክስ ህግ ተገዢ ባልሆኑ ግብር ከፋዮች ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ መንግሥት ከታክስ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዲያገኝ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ ተናግረዋል ።

የገቢ አሰባሰቡን በታክስ አስተዳደሩን ሥርዓት ማዘመን፣ የሺያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል ማድረግ መንግሥት የሚያገኘውን ገቢ እንዲያገኝ ሁሉም በየደረጃው ያለው አመራር የድርሻውን እንዲወጣ የቢሮ ኃላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል።

የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በቀጣይ የተሻለ ገቢ አፈፃፀም ለማምጣት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የጥራት ተደራሽ በሆኑ ገቢዎች ላይ ትኩረት አድርገ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *