











የጎንጋ ህዝቦች የልማትና የትብብር ማህበር ያዘጋጀው 6ኛው የጎንጋ ህዝቦች የልማትና ትብብር ፎረም በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በፎረሙ መክፈቻ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ የጎንጋ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት መጠናከር ለሀገራዊ አንድነት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ግኑኝነቱን በማስፋት በህዝቦች መካከል ህብረብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ የጋራ መልካም ዕሴቶችን በማጉላት እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ማስረሻ በወንድማማች ህንዝቦች መካከል ሁለንተናዊ ትስስርን በማጠናከር የጋራ ባህልና ታሪክ ማሳደግና ማልማት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የህዝቦች እርስበርስ ግኑኝነት መጠናከር ህብረብሔራዊ አንድነት በማጽናት ለሀገራዊ የገዢ ትርክት ግንባታ የጎላ ፋይዳ ያለው በመሆኑ የክልሉ መንግሥት ፎረሙን በአዎንታ እንደሚመለከት የገለጹት አቶ ማስረሻ የክልሉ መንግሥት በቀጣይነትም የጎንጋ ህዝቦች ግኑኝነትና ትብብር እንደሚደግፍ ተናግረዋል።
የጎንጋ ህዝቦች የጋራ ባህልና ታሪክ የነበራቸው ህዝቦች መሆናቸውን የገለጹት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ይሁን እንጂ እነዚህ አንድ ህዝቦች በታሪክ አጋጣሚ በተለያዩ ምክንያቶች ከ4 ምዕት አመታት በላይ ግኑኚነታቸው ተቋርጦ እንደነበረ አንስተዋል።
በ1970ዎቹ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተለኮሰው የአንድነት ችቦ የወንድማማች ህዝቦችን የኃላ ታሪክ በማጥናት ጊዜ ደብቆ እርቀት ገድቦት የነበረው የጎንጋ ቤተሰቦች ማለትም ካፋ ፣ሸካ እና ቦሮ ሺናሻ በ1999 ዳግም ወደ አንድነትና ህብረት ማምጣት መቻሉይ አስረድተዋል።
የጎንጋ ህዝቦች የልማትና የትብብር ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክፈሌ ገ/ማሪያም በበኩላቸው የጎንጋ ህዝቦች ዳግም መገናኘት በወንድማማቾች መካከል ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ዕድል መክፈቱን ተናግረዋል።
ለትብብር ፎረሙ መጠናከር አስተዋፅኦ ያደረጉ አካላትን ያመሰገኑት ስራ አስፈጻሚው በህዝቦች መካከል የተጀመረው ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
በትብብር ፎረሙ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች የተገኙት ሲሆን የሶስቱ ወንድም ህዝቦችን የጋራ ታሪክና ባህል የሚዘክሩ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ቀርቧል።
በቀጣይም በወንድም ህዝቦች ታሪክና ባህል ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግ ተገልጿል።
በዕድገቱ በዛብህ
