
የሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ የህዝብ ትስስርን፣ አንድነትንና የቱሪዝም እንቅስቃሴን ይበልጥ በሚያነቃቃ መልኩ በድምቀት መከበሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ የተከበረውን የኢሬቻ በዓል አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ የህዝብ ትስስርና አንድነትን በሚያጠናክርና የቱሪዝም እንቅስቃሴን ይበልጥ በሚያነቃቃ መልኩ በድምቀት መከበሩን ተናግረዋል።
በሆራ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ከኦሮሚያ ክልል እና ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ብሄር ብሄረሰቦች ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በሚያጠናክር ሁኔታ በድምቀት ማክበራቸውን ገልፀዋል።
በዓሉ በመከባበር፣ በመቻቻል፣ በመፈቃቀርና በደስታ መከበሩንም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ በዓሉን ብዝሃነትንና አብሮነትን በሚያንፀባርቅ መልኩ ማክበር መቻሉንም ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን በድምቀት ማክበሯ በአለም እና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ያላትን ልምድና ተሞክሮ ይበልጥ አጠናክራ እንድትቀጥል የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዓሉ በድምቀት እንዲከበር የመዲናዋ ነዋሪዎች በኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይነትና መስተንግዶ አስደናቂ ተግባር መፈጸማቸውን ከንቲባዋ አስታውቀዋል፡፡
እንግዶችን ተቀብለው በማስተናገድ፣ በዓሉን አብረው በማክበር ወንድማማችነትና እህትማማችነት ጎልቶ እንዲወጣ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
በዓሉ በሰላምና በድምቀት እንዲከበር በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላት ከህዝቡ ጋር በቅንጅትና በትብብር በመስራት የማይተካ ሚና መጫወታቸውን ጠቁመዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓሉ በሰላምና በድምቀት እንዲከበር ላደረጉ የመዲናዋ ነዋሪዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎችና በየደረጃው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ምስጋና አቅርበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
