የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አርብቶ አደር እና ቆላማ አከባቢዎች ጉዳይ ቢሮ የሴክተር ጉባኤ ማካሄድ ጀምሯል

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት አርብቶ አደር እና ቆላማ አከባቢዎች ጉዳይ ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ በየደረጃው ካሉት መዋቅሮች እና ባለድርሻ አካላት ጋር የሴክተር ጉባኤውን በቦንጋ እያካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ዘርፉ በክልሉ ቀላል የማይባል የቆዳ ስፋትና ብዝሀነት በሚገኝበት አከባቢ ላይ ትኩረት አደርጎ የሚሰራ በመሆኑ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ድጋፍ እንደሚሻ አሳስበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ተቋሙ በአርብቶ አደርና ቆላማ አከባቢዎች የመፈጸምና የማስፈፀም አቅም ግንባታ፣ የሰው ኃይልን በትምህርትና ስልጠና እንዲሁም በልምድ ልውውጥ በማብቃት፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በእንስሳትና ሰው ጤና እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ተግባራት ላይ የሚያከናወን በመሆኑ በክልሉ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አንስተዋል።

ባጠቃላይ የአርብቶ አደር ማህበረሰብን በፍላጎት ላይ የተመሠረተ የመንደር ማሰባሰብ በማካሄድ በክልሉ ተመጣጣኝ ልማት ለማምጣት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ስለሚገኝ ተሳታፊዎች ገንብ ሀሳብና አስተያየት በመስጠት ድጋፍ በማድረግ ለውጤታማነቱ መረባረብ እንደሚገባቸው ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንዖት በመስጠት አንስተዋል።

የክልሉ አርብቶ አደርና ቆላማ አከባቢዎች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ በበኩላቸው መንግስት የተለያዩ ፖሊስዎችን፣ ስትራቴጂዎችን እና ፕሮግራሞችን በመንደፍ የረጅም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ ዕቅድ አዘጋጅቶ ተግባራዊ በማድረግ የህዝቡን ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የበለፀገ ማህበረሰብ ለመፍጠር በዘርፉ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል ።

በጉባኤው ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ፣ የክልሉ ም/ር/ መስተዳድር አቶ ማስረሻ በላቸው፣ የክልሉ ብሔረሰቦች ም/ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ መቱ አኮ፣ የክልሉ ፍ/ቤት ፕረዝደንት አቶ ቆጭቶ ገ/ማሪያም፣ የመንግስት ረዳት ተጠሪዎች፣ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የሴክተሩ ባለሙያዎች፣ የወረዳና የዞን አስተዳዳሪዎች ፣ የመንግስት ተጠሪዎችና የዘርፉ ጽ/ቤትና የመምሪያ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ለተሳታፊዎች የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2017 ዓ.ም ዕቅድ በዶ/ር ታጠቅ ብርሃኑ የቢሮ ም/ኃላፊ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግ የወጣው መርሃ ግብር ያስረዳል።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *