




የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከኢፌዲሪ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አዲስ በተሻሻለው የካሳ አዋጅ ቁጥር 1336/2016 ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እና በክልሉ በፌደራል መንግሥት የሚገነቡ የመንገድ ፕሮጀክቶች ያሉበት ደረጃና የክልሉን ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ በክልሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይተዋል።
አዲስ ተሻሽለው የወጣዉ የካሳ አዋጅ ንብረት የመገመት፣ የመክፈል እና የማስነሳት ስራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ ነዉ።
መድረኩ ችግሩን መፍታት የሚያስችል አሰራር ማዘጋጀት በማስፈለጉ እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ እንዲኖራቸው እና በቀጣይ አካሄዶች ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖር በማስፈለጉ ታሳቢ ተደርጎ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው በክልሉ በፌደራል መንግስት የተጀመሩ በርካታ የአስፓልት መንገድ ልማት ፕሮጀክት ግንባታዎች ቢኖሩም ተጠናቀዉ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ከማድረግ አንጻር ጉድለቶች እንደሚታዩ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማጠናቀቅና የጥራት ደረጃቸውን ከማስጠበቅ ጋር ተያይዞ የሚታየው ችግር ሊታረም እንደሚገባ ጠይቀዋል።
ወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ በተለይም የልማት ተነሺዎች ንብረት መቁጠር፣ግምት እና ከቦታ የማስነሳት ሥራ የሚሰራ ቢሆንም ክፊያዉን በወቅቱ ከመፈጸምና ፕሮጀክቶቹን በፍጥነት ወደ ሥራ ከማስገባት አንጻር የሚታዩ ውስንነቶችና ቅንጅታዊ አሠራር ችግሮች ሊፈቱ ይገባል ተብሏል።
በዚህም የሚስተዋለው የብልሹ አሠራርና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ባለድርሻ አካላት በንግግራቸው አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ በክልሉ በፌደራል መንግሥት በርካታ የተጀመሩ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች ቢኖሩም በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ አጠናቀዉ ለህዝብ አገልግሎት ከፍት ከማድረግ አኳያ የሚታየው የአፈጻጸም ችግር ሊታረም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የክልሉ መንግስት የበጀት አቅም በፈቀደ እና ህዝቡን እና ሌሎች አጋር የልማት ድርጅቶችን በማስተባበር እየተከናወነ ያለዉ የልማት ሥራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉ ዋና አፈ ጉባኤው ገልጸዋል።
ዋና አፈ-ጉባኤው አክለውም በፌደራል መንገዶች አስተዳደር በኩል ግምታቸው እና የፕሮጀክት ዶክመንት የተጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች ፈጥነዉ ወደ ሥራ እንዲገቡ ጠይቀዉ ከካሳ ክፊያ ጋር በተያያዘ በፕሮጀክቶች በኩል ትኩረት እንዲሰጥበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በክልሉ በፌደራል መንግስት የሚገነቡ የመንገድ ልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ያለበት ደረጃ የሚገመገም እና የሚከታተል ስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ የሚገባ የአሰራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ሀገራዊ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ተገኝ ገልጸዋል።
ለሥራዉ አፈጻጸም ማነቆ ሊሆኑ የሚችሉ የካሳ ክፊያ እና ሌሎች ጉዳዮችን በየደረጃው ካላቸው ባለድርሻ ተቋማትና አካላት ጋር በቅንጅት ለመፍታት እንደሚሰራ ጠቅሰው የተጀመሩትን ማጠናቀቅና የመንግስት የበጀት አቅም በፈቀደው መጠን አዳዲስ ፕሮጀክቶች በፍትሐዊነት ማስጀመር ላይ ትኩረት ይደረጋል ነዉ ያሉት።
በፍቅር ከበደ
