የግብርና ኤክስቴንሽን የምክር አገልግሎትን ፈጣን ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለጸ

Spread the love

የክልሉ ግብርና ቢሮ የተሳትፏዊ ግብርናና የአየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም (Pact Programme) ለአርሶ አደር መስክ ትምህርት ቤት አመቻቾች ስልጠና በሚዛን አማን እየተካሄደ ይገኛል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የተሳትፏዊ ግብርናና የአየር ንብረት ሽግግር ፕሮግራም ስራ አስኪያጅ አቶ ታመነ ተስፋዬ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ በክልሉ በሴፍትኔት በታቀፉ ዞኖችና ወረዳዎች ላይ የሚሰራ መሆኑን ገልጸው በዚህም በምዕራብ ኦሞ ዞን ማጂ ወረዳ እንዲሁም በዳውሮ ዞን ሎማና ገና ወረዳዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

ስልጠናው በዋናነት የግብርና ኤክስቴንሽን የምክር አገልግሎትን ፈጣን ፣ ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ በታቀፉት ዞንና ወረዳዎች የምግብ ዋስትናን ማረጋጥ መሆኑን ገልጸዋል። በፕሮግራሙ የታፉት ወረዳዎች የምግብ ዋስትናቸውን ያላረጋገጡ ፣ ከፍተኛ ስራ አጥነት ያሉባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን አቶ ታመነ ገልጸው ለ7 ቀናት የሚቆየው የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

አሰልጣኞችም ወደ አርሶና አርብቶ አደሩ ሲወርዱ ችግሮችን በራስ አቅም የመለየት ፣ የመፍታትና የምርምር ሙከራ አቅማቸውን የማሳደግ ስራ ይሰራሉ ብለዋል።

አቶ ታመነ አክለውም በፕሮግራሙ በታቀፉ ወረዳዎች እያንዳዳቸው ከ25 እስከ 30 የሚደርሱ አርሶና አርብቶ አደሮችን የሚያቅፉ 42 የመስክ ትምህርት ቤቶች እንደሚቋቋሙም ገልጸዋል።

ስልጠናው ለ7 ተከታታይ ቀናት የሚቆይ መሆኑንም ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *