የህብረት ሥራ ዘርፍ ሚናዉን በአግባቡ እንዲወጣ ወደ ሪፎርም ሥራ መግባቱ ተገለጸ

Spread the love

የክልሉ ህብረት ስራ ልማት ኤጀንሲ የ9 ወር ዕቅድ አፈጻጸም እና የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በሚዛን አማን እየተካሄደ ይገኛል።

የክልሉ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊና ኢንጂነር አስራት ገብረማሪያም (ዶ/ር) መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት የህብረት ስራ ማህበራት በአለምና በሀገራት ኢኮኖሚና የዜጎችን ህይወት በመቀየር ረገድ ጉልህ ሚና አበርክተዋል ብለዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት እንደ ሀገር የህብረት ስራው ዘርፍ የሚጠበቅበትን ተግባር እንዲፈጽምና ሚናውን እንዲወጣ በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶ ወደ ሪፎርምና የአደረጃጀት ስራ መገባቱን ገልጸዋል። እንደ ክልልም ለዘርፉ ፖለቲካዊ ትርጉም ተሰጥቶ መስራት ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ለውጦችና ውጤቶች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ሪፎርሙ ሙሉ ለሙሉ አለመተግበርና የአፈር ማዳበሪያ ስርጭትና የዕዳ አመላለስ መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ ህብረት ስራ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቀበሌ መንገሻ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ባለፉት አመታት በህብረት ስራ ማህበራት ከታየው የአሰራር ጉድለትና ውጤታማነት አንጻር ሪፎርም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የሪፎርም ሂደቱ እንደ ክልል በጥንካሬ የተገመገመ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አለመደረጉ ሊታረም የሚገባው መህኑን ጠቀለመዋል።

እንደ ክልል 2050 መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራትና 23 ዩኒየኖች እንደሚገኙ ገልጸው በሪፎርሙ የማደራጀት ፣ የማዋሀድና የማፍረስ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አፈጻጸማቸውን መሰረት በማድረግም ማህበራትን በአረንጓዴ ፣ ቢጫና ቀይ የመፈረጅ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

አቶ ቀበሌ አክለውም ከአፈር ማዳበሪያ ሽያጭ ፣ ስርጭትና ዕዳ አመላለስ አንጻር ከቀድሞ ደቡብ ክልል ያደረ 47 ሚሊየን ብር ፣ በ2015/16 የበጀት አመት 189 ሚሊየን ከመዋቅሮች በጀት ተቆራጭ መደረጉን ገልጸዋል። በ2016/17 የበጀት አመት 718 ሚሊየን ብር የአፈር ማዳበሪያ ሽያጭ የተከናወ ሲሆን እስካሁን 337 ሚሊየን ብር ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።

ከኦዲት ስራ አንጻር ከ149 ሚሊየን ብር በላይ ያተረፉ ማህበራት እንዳሉ ሁሉ የኦዲት ጉድለት እና ኪሳራ የተመዘገበባቸው መሰረታዊ ማህበራትና ዩኒየኖች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በመድረኩ ከተለያዩ የክልል ቢሮ የስራ ኃላፊዎች ፣ ከ6ቱም ዞኖች የህብረት ስራ ዘርፍ ኃላፊዎችና የማኔጅመንት አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *