

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ የኾነው የምዕራብ ኦሞ ዞን በወርቅ ክምችት እና በሌሎች የከበሩ ማዕድናት እንዲሁም በተፈጥሮ ሀብት የሚታወቅ አከባቢ ነው።
በዞኑ ከሚገኙ መዋቅሮች መካከል አንዱ ደግሞ የማጂ ቱም ከተማ አስተዳደር ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከሰሞኑ በጥንታዊቷ የማጅ ከተማ ተዘዋውሮ ምልከታ አድርጓል።
የማጂ ከተማ፥ የቀድሞው ካፋ ክፍለሀገር አውራጃ መቀመጫ በመኾን ያገለገለችና ከበርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች ዕድሜ ጠገብና ዝነኛ የነበረ ከተማ ነው።
የማጂ ከተማና አከባቢ በበርካታ የተፈጥሮ ስጦታዎች የበለጸገ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ፣ ከዘጠና ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የኢንግሊዝ ቆንሲላ ጽ/ቤት የነበረው እና ሌሎች ቅርሶች በከተማው ይገኛል።
የማጂ ከተማ በታሪክ አጋጣሚ ሁለት ዓለማትን – አፍሪካ እና አውሮፓን፣ ባህልን እና ዲፕሎማሲን የሚያገናኝ ጥንታዊ ከተማ ነበረ።
በ1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ ማጂ የንግድ እና የዲፕሎማሲ የተሳሰሩበት ስትራቴጂካዊ ከተማ በመኾኑ የውጭ ተጽዕኖ ማዕከል ከኾኑት የኢትዮጵያ አከባቢዎች አንዱም ነበረ።
በ1920ዎቹ ማጂ በኢትዮጵያ ውስጥ የኢንግሊዝ ቆንስላ ጽ/ቤት ከነበረባቸው ጥቂት ቦታዎች አንዱ ሲሆን፣ ይህም በወቅቱ በኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙ የእንግሊዝ ባለስልጣናት መካከል እንደ አገናኝ ሆኖ ማገልገሉን ነው የታሪክ መዛግብት ያስረዳል።
ከዘጠና ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው የቆንስላ ጽ/ቤቱ ህንጻ ፥ በሸክላ እና በአፈር የተሰራ ሲሆን አሁን ላይ የማጅ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አግልግሎት ጽ/ቤት በመኾንም እያገለገለ ይገኛል።
ዛሬም የማጂ ከተማ የዚያን ወቅት የታሪክ ዱካዎች፤ የድሮውን የቆንስላ ጽ/ቤት፣ ዘመን የማይሽረውን ታሪክ እና በአንድ ወቅት አህጉራትን አቋርጠው ወደዚያ ለመድረስ ያቀኑት ሰዎች ታሪክ በሹክሹክታ ታወራለች።
ማጂ የሚትታወቅባቸው የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ፀጋዎችን እና አኩሪ ታሪክን በውስጧ ሸሽጋ የያዘች ከተማ ነች።
ከተማዋ ለኢንቨስትመንትና ለኑሮ ምቹ የአየር ጸባይና የመሬት አቀማመጥ እንዲሁም ሌሎች ገጸበረከቶችን በጉያዋ አቅፋ የያዘች በመኾኗ አልሚ ባለሀብቶችን የሚትጣራ ድንቅ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራም ናት፡፡
የድልብ ታሪክ ባለቤት የኾነችሁ የማጂ ከተማ ፣ እንግዳ ተቀባይ ስስት የሌለባት ከምድሯ የረገጠ የሚከብርባት ከተማ ናት።
በዙሪያዋ በሚገኙ ሳይ፣አዲካስ፣ቱምና ዙሪያዋ ቀበሌዎች የወርቅ እና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት፣ የኦሞ ተፋሰስን ይዞ የብረት ማዕድናት የሚገኝበት አከባቢ እንደኾነች የሚነገርላት የማጂ ከተማ አሁን በሠላምና የልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች።
በጭጋጋማ ተራሮች የተሸፈነው የጥንታዊቷ ማጂ ከተማ ውበት፣ ታሪክ እና ቅርስ ወደ አደባባይ መውጣትና መድመቅ ጀምሯል።
በዕድገቱ በዛብህ
