“ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሀሳብ ተነስቶ ለዓለምአቀፍ ለውጥ የሚሰራ ብርቱ ኃይል ወደመሆን ተሸጋግሯል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

Spread the love

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሪዮ ዲ ጄኒሮ እየተካሄደ በሚገኘው 17ኛው የብሪክስ ጉባኤ የሰላም፣ የጸጥታ እና ዓለምአቀፍ አመራር መድረክ መክፈቻ ላይ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም ስኬታማ ትብብርን ለማስቻል አፀፋዊ መተማመንን የሚያሳድጉ ዓለምአቀፍ ተቋማት የመኖርን አጣዳፊነት አንስተዋል።

ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት የጋራ ደኅንነትን እና ሁሉን አካታች ብልጽግናን ለማምጣት ይረዳ ዘንድ የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅራቸው ምሉዕነት ባለው መልክ የሚሻሻልበትን ሁኔታም አፅንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በይፋ ወደ ብሪክስ የተቀላቀለችው በ2015 ዓ.ም ሲሆን ኢኮኖሚያዊ ወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ፍትኃዊ የሆነ፣ እኩልነት የሚሰፍንበት ብዝኃ ዋልታዊ ዓለምን ለመፍጠር ከሚተጉ ሀገራት ጋር በእኩል ደረጃ የተሰለፈችበት ስብስብ ነው ብለዋል።

እንደ ብሪክስ አባልነቷ ኢትዮጵያ እነዚህ ጥረቶች እንዲሳኩ በተለይም በዓለምአቀፍ ውሳኔ ሰጪ መድረኮች ለአዳዲስ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ሰፋ ያለ ውክልና በሚገኝበት ሁኔታ ላይ በንቃት አስተዋፅኦ ታደርጋለች ነው ያሉት።

የብሪክስን እያደገ የመጣ ተፅዕኖ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሀሳብ ተነስቶ ለዓለምአቀፍ ለውጥ የሚሰራ ብርቱ ኃይል ወደመሆን ተሸጋግሯል ብለዋል። አዳዲስ አባላት በመጨመራቸውም የጋራ ድምፃችን የበለጠ ይጠናከራል። የጋራ ዓላማችን የበለጠ ይጠራል። አቅማችንም ይሰፋል ማለታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *